የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ነገ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ነገ ይጀመራል
ኢዜአ ታህሳስ 24 /2012 የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በሚካሄዱ ጨዋታዎች ይጀመራል። 10 ክለቦች የሚሳተፉበት አራተኛው ፕሪሚየር ሊግ ታህሳስ 18 እና 19 ቀን 2012 ዓ.ም መጀመር የነበረበት ቢሆንም የተወሰኑ ክለቦች በዝግጅት ማነስ ምክንያት ሊጉ በአንድ ሳምንት እንዲራዘም በመጠየቃቸው ነው። ሊጉ ነገ የሚጀመር ሲሆን በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከጠዋቱ 3፡00 መከላከያ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ከረፋዱ 4፡30 የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከአዲሱ የሊጉ ተሳታፊ ሚዛን አማንና ፌዴራል ፖሊስ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታ ከረፋዱ 5፡30 ላይ ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያ በክልል ከተሞች ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከጠዋቱ 3፡00 ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከጎንደር ከተማ እንዲሁም ከረፋዱ 5፡00 ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ይጫወታሉ። አምና በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የነበረው ድሬዳዋ ከተማ ክለቡን ያፈረሰ ሲሆን ሚዛን አማን ክለብ በማቋቋም በዘንድሮው የሊግ ውድድር የሚሳተፍ አዲስ ክለብ ነው። መከላከያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከዚህ በፊት የተካሄዱት የሊግ ውደድሮች አሸናፊ ናቸው። ታህሳስ 11 ቀን የ2012 ዓ.ም በተካሄደው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የቅድመ ውይይትና እጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት በባለፈው ዓመት ፕሪሚየር ሊግ በስፖርታዊ ጨዋነት የታዩ ግድፈቶች በዘንድሮው የውድድር ዓመት እንዳይደገሙ ሁሉም አካል በሃላፊነት እንዲሰራ መግባባት ላይ ተደርሷል።