በሞጣ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ምክር ቤት ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ክልሉ ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በሞጣ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ምክር ቤት ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ክልሉ ገለፀ
ኢዜአ ታህሳስ 23 / 2012 የአማራ ክልል መንግስት በሞጣ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዩች ጠቅላይ ምክር ቤት ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ገለፀ። በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ ባለፈው ሳምንት በመስጂዶች ላይ የተፈጸመውን የቃጠሎ ጥቃት ተከትሎ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዩች ጠቅላይ ምክር ቤት የተሰየመው አጣሪ ኮሚቴ አባላት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። አጣሪ ኮሚቴው ታሕሳስ 10 ቀን 2012 ወደ ስፍራው በማቅናት ከሞጣ ከተማ የሙስሊሙ ማሕበረሰብ አባላትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየቱን ገልጿል። የኮሚቴው አባል ኡስታዝ በድሩ ሁሴን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የአማራ ክልል አመራሮች ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ለተላከው አጣሪ የልኡካን ቡድን መልካም ትብብር አድርጓል። በሞጣ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዩች ጠቅላይ ምክር ቤት ያቀረባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን እንዳረጋገጠላቸውም አመልክተዋል። መንግስት የተከሰቱትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ኮሚቴው መገንዘቡንም አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት ክልሉ በመንግስት እና የፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በጥቃቱ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን ኮሚቴው ለመረዳት መቻሉንም ጠቁመዋል። የከተማው ህዝብ ከልኡካን ቡድኑ አባላት ጋር በተወያየበት ወቅትም በቃጠሎው የወደመውን መስጅድና የንግድ ማዕከላት የአማራ ክልል መንግስት መልሶ እንዲገነባ ጠይቋል ብለዋል። በተጨማሪም ህዝቡ በከተማው አስተዳደር የፀጥታ ክፍል ላይ እምነት እያጣ መሆኑን ማንሳቱ'ንም አክለዋል። በመሆኑም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን የፀጥታና የደህንነት ዋስትና እንዲሰጠው ማሳሰቡንም አመልክተዋል። ሌላው የኮሚቴው አባል ሽህ ኑረዲን ደሊል በበኩላቸው መንግስት የሕግ የበላይነትን ማስከበር አለበት ሲሉ አሳስበዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም በተለይ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት የመብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ማውገዝ እንደሚገባቸው ነው የኮሚቴው አባላት ያስገነዘቡት።