የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አራተኛ ቀን ውሎ የፍጻሜ ውድድር ውጤቶች - ኢዜአ አማርኛ
የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አራተኛ ቀን ውሎ የፍጻሜ ውድድር ውጤቶች
ኢዜአ ታህሳስ 22 /2012 በኢትዮጵያ የታዳጊዎች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የአራተኛ ቀን ውሎ ስድስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል። ከታህሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሻምፒዮናው በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም እየተካሄደ ይገኛል። በፍጻሜ ውደድሮቹ ደብርብርሃን የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ተወዳዳሪዎች በሶስቱ፣ የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪዎች በሁለቱ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በአንዱ ውድድር ማሸነፍ ችለዋል። ከ18 ዓመት በታች ሴት የሶስት ሺህ ሜትር መሰናክል ከደብርብርሃን የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የተሳተፈችው አትሌት መልክናት ውድ 9 ደቂቃ ከ28 ሴኮንድ ከ8 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት አሸንፋለች። የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪዋ አትሌት ጫልቱ በዳዳ 9 ደቂቃ ከ33 ሴኮንድ ከ6 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ፣ አትሌት አሳየች አድማሱ ከተንታ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል 9 ደቂቃ ከ37 ሴኮንድ ከ2 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥታለች። ከ18 ዓመት በታች ወንድ 400 ሜትር መሰናክል አትሌት ይሁኔ ጌትነት ከደብረብርሃን የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል 53 ሴኮንድ ከ4 ማይክሮ ሴኮንድ አሸናፊ ሆኗል። ሌላኛው የደብረብርሃን የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ተወዳዳሪ አትሌት አስፋው ተሾመ በ53 ሴኮንድ ከ6 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ሲወጣ አትሌት ስንታየሁ የሚና ከደቡብ ክልል 54 ሴኮንድ ከ9 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ከ16 ዓመት በታች ወንድ አንድ ሺህ ሜትር የደቡብ ክልል ተወዳዳሪ የሆነው ቶፊቅ በዳታ 2 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ ከ6 ማይክሮ ሴኮን አሸንፏል። አትሌት ምስጋኑ ብርሃኑ ከኦሮሚያ ክልል 2 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ከ1 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ፣ ሃይለማርያም ገብረዮሐንስ ከትግራይ ክልል 2 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ከ6 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ወጥቷል። ከ18 ዓመት በታች ሴት አሎሎ ውርወራ አትሌት አማረች አለምነህ ከደብረብርሃን የአትሌቲክ አሰልጣኝ ማዕከል 11 ነጥብ 01 ሜትር በመወርወር አሸናፊ ስትሆን፤ አትሌት ዝናሽ ማቲዮስ ከኦሮሚያ ክልል 10 ነጥብ 66 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ወጥታለች። ሰተዋ ሻሽ ከደቡብ ክልል 10 ነጥብ 20 ሜትር ወርውራ ሶስተኛ ደረጃን አግኝታለች። ከ18 ዓመት በታች ወንድ የጦር ውርወራ አትሌት ሰንበቶ ኢሚሩ 63 ነጥብ 01 ሜትር በመወርወር አሸናፊ ሲሆን አትሌት አብዱ ኢብራሂም ከደብረብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል 55 ነጥብ 53 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። አትሌት ኦጅሉ ድድሙ ከጋምቤላ ክልል 52 ነጥብ 79 ሜትር በመወርወር ሶስተኛ ወጥቷል። ከ16 ዓመት በታች ሴት የርዝመት ዝላይ የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪዋ አትሌት ታረቀች ኡዶ 5 ነጥብ 36 ሜትር በመዝለል አሸናፊ ስትሆን አትሌት ጆክ ኡባንክ ከጋምቤላ ክልል 4 ነጥብ 71 ሜትር በመዝለል ሁለተኛ ወጥታለች። ሌላኛዋ የጋምቤላ ክልል ተወዳዳሪ አትሌት አኩኒ አባላ 4 ነጥብ 69 ሜትር በመዝለል ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። ከፍጻሜ ውድድሮቹ በተጨማሪ ከ18 ዓመት በታች ወንድና ሴት በተመሳሳይ የ200 ሜትር የማጣሪያ ውድድር ተካሄዷል። ሻምፒዮናው ነገም ሲቀጥል ስምንት የፍጻሜና ሁለት የማጣሪያ ውድድሮች እንደሚካሄዱም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የኢትዮጵያ የታዳጊዎች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ከነገ በስቲያ ይጠናቀቃል።