ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ ቀጣይ ጨዋታዎች ከነገ ጀምረው ይካሄዳሉ

ኢዜአ ታህሳስ 22 /2012 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ ይካሄዳሉ። ነገ በስታዲየም ግንባታ ምክንያት የሜዳ ጨዋታዎቹን በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረገ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታል። በአምስት ነጥብ 13ኛ ደረጃላይ የሚገኘውና እስካሁን በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው ሰበታ ከተማ ባለፈው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር 3 ለ 3 የአቻ ውጤት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ይጫወታል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ሰበታ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም እስካሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ አልቻልም፤ በሁለቱ ተሸንፏል በቀሪዎቹ አቻ ወጥቷል። በተመሳሳይ አምስት ነጥብ ከተጋጣሚው በግብ ክፍያ ተሽሎ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ባለፈው ሳምንት በሜዳው በወልቂጤ ከተማ ከገጠመው ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የነገው ጨዋታ ጥሩ አጋጣሚ ይሆንለታል። በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታው ሲዳማ ቡናን ካሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ አቻ ሲወጣ በሁለቱ ሽንፈት ገጥሞታል። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘውን ሀድያ ሆሳዕናን ያስተናግዳል። በክልል ከተሞች በትግራይ ስታዲየም የሊጉ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሀዋሳ ከተማ፣ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከባህርዳር ከተማ፣በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማ ከጅማ አባ ጅፋር፣ በይርጋለም ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከድሬዳዋ ከተማና በዝዋይ ሼር ኢትዮጵያ ሜዳ ወልቂጤ ከተማ ከስሑል ሽረ ጋር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። እሁድ ታህሳስ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምናው የሊጉ አሸናፊ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ጋር ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት የሚያደርጉት ጨዋታ በሳምንቱ የሚጠበቅ ጨዋታ ነው። በሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሴርዳን ዚሆጂሆቭ የሚሰለጥነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰበታ ከተማን ካሸነፈበት ጨዋታ ውጪ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለ ሲሆን በስድስት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 14 ጊዜ ፕሪሚየር ሊጉን በማሸነፍ ስኬታማ ክለብ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለው የዋንጫ ተፎካካሪነት አንጻር የዘንድሮ አጀማመሩ ደካማ የሚባል ነው። የእሁዱ ጨዋታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነትና ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ለመመለስ ወሳኝ ጨዋታ ነው። በአንጻሩ በሊጉ 10 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውና በአሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ የሚሰለጥነው መቐለ ሰብዓ እንደርታ እስካሁን በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሶስቱን አሸንፎ በአንዱ አቻ ወጥቶ በአንዱ ተሸንፏል። ለመቐለ ሰብዓ እንደርታ የእሁዱ ጨዋታ የባለፈው ዓመቱን የሊጉን ክብር ለማስጠበቅ ለሚያደርገው ጉዞ ወሳኝ የሚባል ጨዋታ ነው። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ወልቂጤ ከተማ በሜዳ እድሳት ምክንያት ጨዋታዎችን በሌላ ሜዳ እያደረጉ የሚገኙ ክለቦች ናቸው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና መቐለ ሰብዓ እንደርታ በተመሳሳይ 10 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል። ሲዳማ ቡና በዘጠኝ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ስሑል ሽረ በአምስት ነጥብ፣ድሬዳዋ ከተማ በአራት ነጥብ እና ሀድያ ሆሳዕና በሁለት ነጥብ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነትን የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም፣ ማሊያዊው የባህርዳር ከተማ ተጫዋች ማማዱ ሲዲቤና ሌላኛው የባህርዳር ከተማ ተጫዋች ፍጹም አለሙ፣የሀዋሳ ከተማው ብሩክ በየነና የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ በተመሳሳይ አራት ግቦች እየመሩ ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም