በሀሳብ መሸናነፍን በሰላማዊ መንገድ መቀበል የስልጣኔ መገለጫ ነው - የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በሀሳብ መሸናነፍን በሰላማዊ መንገድ መቀበል የስልጣኔ መገለጫ ነው - የኃይማኖት አባቶች
ኢዜአ፤ ታህሳስ 23/2012 በሀሳብ መሸናነፍን በሰላማዊ መንገድ መቀበል የስልጣኔ መገለጫ መሆኑን የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ። በመጪው ግንቦት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅም ለመራጩ ህዝብና ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያናት ህብረት መሪዎች በወቅታዊ የአገሪቷ የሰላም ሁኔታ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። በዚሁ ጊዜ በተለይ በምርጫ ጊዜ በሰለጠኑት አገሮች ያለውን የሀሳብ ፍጭትና የመነጋገር ባህል መቅሰም እንደሚገባ ገልጸዋል። የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የቅዱስ ፓትሪያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሊቀ-ጳጳስ ብጹህ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መራጩ ህዝብና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል። እንደ ብጹህ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ገለጻ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝቡ የሚበጁ ሀሳቦችን በሰላማዊ መንገድ ማስተዋወቅ አለባቸው። መራጩ ህዝብም በሃቀኝነት በታማኝነት ድምጹን መስጠትና ውጤቱንም በጸጋ መቀበል ይገባዋል። የአገሪቷ ምርጫውን በሰላም ማጠናቀቅ ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያገኙት የሰላም የኖቤል ሽልማት ለአገሪቷና ለህዝቦቿ የሚገባ መሆኑን ማረጋገጫ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሰላምና ትብብር ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሃመድ በበኩላቸው ለምርጫው ሰላማዊነት መራጩም ሆነ ተመራጩ በልበ ሰፊነት መስራት አለባቸው ነው ያሉት። በሁከትና ብጥብጥ ሀሳብን መግለጽም ለአገር የሚጠቅም ፍሬ ነገር የማይገኝበት በመሆኑ ከስሜታዊነት ወጥቶ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለ አገር ለማስረከብ መትጋት አለብን ብለዋል። የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ-ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡን በኃይማኖትና በብሄር ከሚከፋፍሉና ጥላቻን ከሚፈጥሩ ቅስቀሳዎች ሊቆጠቡ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት። ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግም በአገሪቷ እየተስተዋሉ ያሉ አንዳንድ ግጭቶችን በአፋጣኝ ማስቆም ተገቢ መሆኑንም አንስተዋል። ምርጫ የዜጎችንም ሆነ የአገርን የወደፊት ዕጣ-ፈንታ የሚወስን በመሆኑም መራጩ ህዝብ ስለሚመርጠው ፓርቲ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ከወዲሁ መስራት ይገባልም ብለዋል። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የሲቪክ ማህበራትና ምሁራንም ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኃይማኖት መሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።