በከፋፋይና ያረጀ እሳቤ የሚመራው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል የመወሰን አቅም የለውም- የፖለቲካ ልሂቃንና የህግ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በከፋፋይና ያረጀ እሳቤ የሚመራው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል የመወሰን አቅም የለውም- የፖለቲካ ልሂቃንና የህግ ምሁራን
ኢዜአ ታህሣስ 23 /2012 በከፋፋይና ያረጀ እሳቤ የሚመራው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል የመወሰን አቅም የለውም ሲሉ የፖለቲካ ልሂቃንና የህግ ምሁራን ተናገሩ። የኢህአዴግ ውህደት ህጋዊ መስመርን የተከተለ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን ጋር በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂዷል። የኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ ምህዳርና ሰላም ደግሞ የውይይቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። የህግ ምሁሩ ዶክተር ዮናስ ተስፋ "ላለፉት 27 ዓመታት አብዮታዊ ዴሞክራሲ ትክክለኝነትና ስህተት እንዲሁም እውቀት የሚለካበት ሚዛን ሆኖ አገልግሏል" ብለዋል። በዚህም የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት በዚሁ ሚዛን ልኬት ወዳጅ እና ጠላት ተብለው ተፈርጀው ቆይተዋል ነው ያሉት ዶክተር ዮናስ። ስርዓቱ እንደስኬት የሚቆጥረው የኢኮኖሚ እድገት አስከፊ የሆነውን የዜጎች የድህነት ምጣኔን እንኳ በወጉ ማሻሸል እንዳልቻለም አብራርተዋል። መንግስት "የተቋማት ሪፎርም አንገብጋቢ ጉዳዬ" ነው ሲል በተደጋጋሚ መግለጹን በአመክኒዎነት በማንሳት። የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ሙሉብርሃን ኃይሉ በበኩላቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ አንዱን ተዋናይ ሌላኛውን ደግሞ ተመልካች ማድረጉን ይናገራሉ። ነገር ግን ሀገር መለወጥ የሚችለው እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ድርሻ ማበርከት ሲችል ነው ብለዋል። የፖለቲካ እሳቤም ሆነ ፍልስፍና ከዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር አብሮ መሄድ እንዳለበት ገልጸው፤ ከዚህ አንጻር የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ከመታመም አልፎ ወደእርጅና መሸጋገሩን አብራርተዋል። የኢፌዴሪ ህገ መንግስትና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር በተቃራኒ ጎዳና ሲጓዙ ነበር የሚሉት ደግሞ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አመራር አቶ ታዬ ደንደኣ ናቸው። በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ምህዳር ስር በፍርድ ቤቶች ሲፈጸም የነበረውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የጠላትና ወዳጅ ፍረጃ አካሄደን በአስረጂነት አንስተዋል። ይህ የፖለቲካ አስተሳሰብ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ እንደማይመጥንም ተናግረዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ መዳኛ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቻ ነው ብሎ መታገል የኢትዮጵያን ህዝብ የአስተሳሰብ ደረጃ ከ20 ዓመት በላይ ወደ ኋላ የተመለሰ አድርጎ መቁጠር መሆኑን በመግለጽ። በተያያዘ ዜና የፓርላማ አባላት በኢህአዴግ ስም በመወከላቸው ብልጽግና ፓርቲ መንግስትን የመምራት ቅቡልነት የለውም የሚለው ሃሳብ በህግ እንዴት ይታያል ሲሉ ኢዜአ ለህግ ምሁሩ ዶክተር ዮናስ አንስቶላቸዋል። ዶክተር ዮናስ በምላሻቸው" ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ አንድ የተዋሃደ ፓርቲ ለመዋሃድ የወሰኑ ፓርቲዎችን መብትና ግዴታ ይወስዳል ነው" ያሉት። ይህ በፓርላማ ያላቸውን ወንበርን ጭምር እንደሚያካትትም ገልጸዋል። የኢፌዴሪ ህገመንግስት የተዋሃደ ፓርቲ የፓርላማ ወንበሩን ያጣል የሚል ድንጋጌ እንደሌለው በመጠቆም። እህት ድርጅቶቹ ጥምረቱን ከማፍረስ በላቀ ወደ መዋሃድ በመሄዳቸው መንግስት ሆኖ አገር የማስተዳደሩ ኃላፊነት ላይ ምንም አይነት የተለየ ጉዳይ አይፈጥርም ሲሉም ተናግረዋል። የፓርላማ አባላቱ ውህደቱን ባይቀበሉ እንኳ የግል ተመራጭ ሆነው ዘመናቸውን ማጠናቀቅ የሚችሉ መሆኑንም ህግን አስደግፈው ማብራሪያ ሰጥተዋል።