ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ
ኢዜአ ታህሳስ 23/2012 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ። የቤንች ሸኮ ዞን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአካባቢው የተቀዛቀዘው ድጋፍ ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ተወያይቷል።
የምክር ቤቱ አስተባባሪ አቶ ታጋይ ገብሬ በውይይቱ ወቅት "የግድቡ ዋንጫ ወደዞኑ ከመምጣቱ በፊትና ከዛም በኋላ ህብረተሰቡ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል" ብለዋል።
በዞኑ 74 ሚሊዮን 400ሺህ ብር ከህብረተሰቡ ከተገባው ቃል 37 ሚሊዮን ብር ብቻ ገቢ መደረጉን አመልክተዋል።
የግንዛቤና ቅስቀሳ ሥራ በመዳከሙ ለአፈፃፀሙ ማነስ ምክንያት እንደሆነም ጠቁመዋል።
ቃል የገቡ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች እንዳሉ ተናግረው በቀጣይ ወራት ለመሰብሰብ ታቅዷል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ አቶ ቀበሌ መንገሻ በበኩላቸው "የህዳሴው ግድብ ከምጣኔ ሀብት ፋይዳው ባሻገር ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር ሚናው የጎላ ነው "ብለዋል።
መላ ኢትዮጵያውያን ተባብረው እየሰሩት የሚገኝ ታላቅ ፕሮጀክት ነው።
የዞኑ ህብረተሰብ ከዚህ ቀደም ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየ ሁሉ በቀጣይም እገዛውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
" አስተዳደሩ የህብረተሰቡ ድጋፉ እንዲቀጥል እስከ ቀበሌ ድረስ በትኩረት ይሰራል " ያሉት ምክትል አስተዳደሪው በቀጣይ ወራትም ቃል ተገብቶ ገቢ ያልሆነ ገንዘብን ለማስገባት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ከውይይቱ ከተሳታፊዎች መካከል ባሻ ደምሴ ካዝንቴት "ከዚህ በፊት ይደረግ የነበረው የማስተዋወቅ እንቅስቃሴ አለመቀጠሉ በተሳትፎ ላይ መቀዛቀዝ አምጥቷል "ብለዋል።
ህብረተሰቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ግንዛቤ የማስጨበጡ ስራ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት እየተገነባ የሚገኘው ግድብ ከዳር እንዲደርስም ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ውይይት የተካሄደው ከታህሳስ 21/2012ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚዛን አማን ከተማ ነው።