የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ህዝብን የማረሩ ችግሮችን ለመቅረፍ በጥናት ላይ የተመሠረተ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ህዝብን የማረሩ ችግሮችን ለመቅረፍ በጥናት ላይ የተመሠረተ እርምጃ መውሰድ ተጀመረ
ታህሳስ 23/2012 በባህርዳር ከተማ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በየጊዜው እየተባባሱ መምጣት ህዝቡን ለምሬት እየዳረጉ ይገኛሉ። ከተማ አስተዳደሩ አንድ ግብር ሃይል በማቋቋም ካለፈው ህዳር ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ ባደረገው ጥናት የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደልና የህግ የበላይነት አለመከበር ህዝቡን ያማረሩ ችግሮች ሆነው ተለይተዋል። የከንቲባ አስተባባሪ ኮሚቴው የተለዩ ችግሮችን በመገምገም ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድ ብቻውን ችግሩን የማይፈታ ሆኖ በመገኘቱ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የጋራ መግባባት ተደርሶ ስራ ተጀምሯል። በዚህም የከተማ አስተዳደሩ መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት በተወሰደ እርምጃ አምስት ሰራተኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። ከመሬት ጋር በተያያዘም መሬትን ያለአባብ አውለዋል ተብለው የሚጠረጠሩ አካላትን ለይቶ ለህግ ለማቅረብ የተቋቋመው አጣሪ ግብረ ኃይል ስራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ህገወጥ የመሬት ወረራን ህጋዊ መስመር ለማስያዝም እስከ 2011 የተገነቡ ቤቶችን አስተዳደሩ በጥናት ለመለየት እየሰራ ሲሆን በ2012 ዓ.ም ደግሞ አዲስ እንዳይገነባ፣ ተገንብቶ ሲገኝ ተከታትሎ የማፍረስ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በቀጣይም በስራ እጥነትና በኑሮ ውድነት ዙሪያ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አሰራሮችን የመፈተሽ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። የከተማ አስተዳደሩ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገሩ ሙሉ በበኩላቸው ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሆን ብለው ህዝብን የሚያጉላሉ አጥፊዎችን በመለየት በህግ ቁጥጥር ስር የማዋሉ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። እስካሁንም በመንገድና ትራንስፖት ጽህፈት ቤት የጽሁፍና የተግባር ፈተና የሚፈትኑና ውጤት የሚሞሉ እንዲሁም መንጃ ፈቃድን በገንዘብ በማደል የተጠረጠሩ ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል። ከመሬትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሉትን ችግሮችም እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ የጀመረውን የማጣራት ስራ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በየተያዙት ላይም ክስ ለመመስረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከመንገድና ትራንስፖርት ተገልጋዩች መካከል ወጣት ተንሳው ሙጨዬ በሰጠው አስተያየት ከአምስት ዓመት በፊት መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ቢመላለስም በህጋዊ መንገድ ማግኘት ባለመቻሉ 3 ሺህ 500 ብር ከፍሎ መንጃ ፈቃዱን ማግኘት እንደቻለ ገልጿል። ዛሬም የንብረት ዝውውር ለማድረግ ቢመላለስም ምንም አይነት አገልግሎት ሳያገኝ አራተኛ ቀን ማስቆጠሩን ጠቅሶ፤ በሰራተኞች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ተናግሯል፡፡ የበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አምሳሉ ብርሃኑ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በመንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።