ቀጥታ፡

በአክሱም ከተማ የሚገኙ ጥንታዊ ህንጻዎች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው

ታህሳስ 23/2012 በአክሱም ከተማ የሚገኙ ጥንታዊ ህንጻዎች ለከፍተኛ ጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸው የአክሱም አለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳዳሪ ገለፁ፡፡

በአክሱም ከተማ በዓለም ቅርስነት መዝገብ ሰፍረው የሚገኙና 200 አመታት በላይ እድሜ ያላቸው ጥንታዊ ህንጻዎች ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት ዩኔስኮ/ በቅርሶቹ አጠባበቅ እና ጥገና ላይ የሚታየውን ክፍተት አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተገልጿል፡፡

የአክሱም አለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳዳሪ አቶ ሚኪኤለ ተስፋይ ለኢዜአ እንደገለጹት ''ጥንታዊ የሆኑ ህንጻዎች ከመፍረስ ለማዳን የጋራ ጥረት ያስፈልጋል'' ብለዋል።

አክሱም በአለም ህዝቦች የምትታወቅባቸው ጥንታዊ ህንጻዎች ዛሬ ላይ እየፈረሱ በምትካቸው ዘመናዊ ቤቶች እየተገነቡባቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ይህ አሰራር ደግሞ ጥንታዊ ቅርሶቹን የሚያጠፋ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

''ጥንታዊ ቤቶችን በማፍረስ በምትካቸው አዳዲሰ ዘመናዊ ቪላ ቤቶች እንዳይገነቡ ዩኔሰኮ አስጠንቅቋል'' ያሉት  አቶ ሚኪኤለ የከተማ መስተዳድር ህገ ወጥ ግንባታዎችን ማሰቆም እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍጹምብርሃን በበኩላቸው በዩኒስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ጥንታዊ የአክሱም ቤቶች /የኪነ ህንጻ ጥበቦች/ የቱሪስት መስህብ ሆነው በማገልገል ላይ እንደሚገኙና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ህንጻዎቹ የታሪክና የማንነት መገለጫ መሆናችውን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ  በአጠባበቁ በኩልም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ  ተከታታይ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በቅርሶቹ አካባቢ የሚካሄዱ ህገ ወጥ የቤቶች ግንባታ ለማስቆምም ከክልሉ ምክር ቤት ጋር በመነጋገር መመሪያ እንዲዘጋጅለት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመፍረስ አደጋ የተደቀነባቸው ከ200 በላይ ጥንታዊ ቤቶች ጥገና ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንና ለጥገና ስራው 2 ሚሊዮን ዩሮ ከጣሊያን መንግስት በድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።

የከተማው መስተዳድር የምክር ቤት አባላት ጥንታዊ ህንጻዎቹ ያሉበት ሁኔታ ለማወቅ የመስክ ምልከታ ማድረጋቸውና እየደረሰባቸው ያለውን ጉዳት ለመከላከል መምሪያ እንደሚዘጋጅላቸው መወሰኑን ያስታወቁት ደግሞ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ሓዱሽ ገብረመድህን ናቸው።

በተለይ ነባር ቅርሶችን የሚያደበዝዙና ጉዳት የሚያደርሱ ህገ ወጥ ቤቶች ግንባታ ፍቃድ አሰጣጥና አሰራር እንዲቆም መምሪያ በማዘጋጀት የክትትልና ቁጥጥር አሰራሩ እንደሚጠናከርም ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቅርሶች ጥበቃ፣ ጥገናና እንክብካቤ ከከተማው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ አቶ ሓዱሽ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም