ቀጥታ፡

ዞኑ ለሁለት እንዲደራጅ መወሰኑ መንግስት የህዝቦችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ ትልቅ ማሳያ ነው - አስተያየት ሰጪዎች

ኢዜአ  ታህሳስ 23/2012 የባሌ ዞን በሁለት ዞኖች እንዲደራጅ መወሰኑ መንግስታዊ አገልግሎቶችን በአቅራቢያቸው ለማግኘት እንደሚያስችላቸው አስተያየታቸውን የሰጡ የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ውሳኔው መንግስት አግባብ ያለውን የህዝቦችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈታ ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል፡፡ የባሌ ዞን በሁለት ዞን እንዲደራጅ የክልሉ ካቢኔ ውሳኔ ማሰለፉን በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል ሀጂ ኡስማን ከዲር እንደገለጹት ከዚህ በፊት ከዞኑ የቆዳ ስፋት የተነሳ ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ሮቤ መጥቶ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በተለይ ከዞኑ ቆላማ ወረዳዎች አካባቢ ወደ ባሌ ሮቤ ለመምጣት ያለው ርቀት ከመሰረተ ልማት አለመሟላት ጋር ተዳምሮ ሁኔታዎችን አስቸጋሪ አድርጎ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ መንግስት የአካባቢው ማህበረሰብ ለዘመናት ያነሳ የነበረውን ችግር በራሱ መንገድ በማጣራት ዞኑ ለአስተዳደር እንዲያመች ለሁለት እንዲከፈል መወሰኑ መንግስት ለህዝቦች ጥያቄ ያለውን ከበሬታ ማሳያ ነው፡፡ ''ከዚህ በፊት መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት የዞኑ ዋና ከተማ ለመድረስ እስከ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዝ ግድ የሚሆንባቸው የአርብቶ አደር ወረዳ ነዋሪዎች ነበሩ'' ያሉት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ የአገር ሽማግሌ ሼህ አብደላ መሐመድ ናቸው፡፡ የክልሉ መንግስት የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ውሳኔ ማሳለፉ ህዝቡ ከመንግስት የሚፈልገውን አገልግሎት በአቅራቢያው በፍጥነት እንዲያገኝ ከማድረጉም ባሸገር የተጓደሉ መሰረተ ልማቶችም እንዲሟሉ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ አቶ ግርማ አበባ በበኩላቸው ውሳኔው መንግስት የሚያስተዳድረውን ህዝብ የልብ ትርታ በማዳመጥ ጥያቄውን ደረጃ በደረጃ እየፈታ መሆኑን ማሳያ ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥቷል፡፡ ዞኑን ለሁለት መከፈሉ ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት አስተያየት ሰጪው ለአስተዳደር የሚያስፈልጉ መዋቅሮችና መሰረተ ልማት የማሟላት ተግባር ቀጣይ ስራ መሆን እንዳለበት ጠይቋል፡፡ የመሠረተ ልማት እጥረት የሚታይባቸውንና ከዞኑ ዋና ከተማ በርቀት ላይ የሚገኙ ቆላማ የአርብቶ አደር ወረዳዎችን የመንገድ፣ የውኃ፣ የመብራትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት የመንግስት ቀጣይ የቤት ስራ መሆኑን ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ካቢኔ የቀረበለትን ጥናት መነሻ በማድረግ ውይይት ካካሄደ በኋላ የባሌ ዞን የነበረው፤ ምስራቅና ምእራብ ባሌ ዞን ሆኖ እንደ አዲስ እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የክልሉን ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በውሳኔው መሠረትም የምእራብ ባሌ ዞን ዋና ከተማ ሮቤ፤ የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና ከተማ ደግሞ ጊኒር እንዲሆን የቀረበው ምክረ ሀሳብም በሙሉ ድምጽ መጽደቁ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም