የዓድዋ-- ራማ የአስፓልት መንገድ ግንባታ መጓተቱ ቅሬታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ-- ራማ የአስፓልት መንገድ ግንባታ መጓተቱ ቅሬታ ፈጥሯል
ኢዜአ ታህሳስ 23/2012 የዓድዋ-- ራማ የ40 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ በመጓተቱ የአካባቢው ነዋሪዎችና አሽከረካሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የመንገዱ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም ድክመት እንዳለበት ተቋራጩ ከተገመገመ በኋላ መሻሻል ማሳየቱን አመልክቷል።
በትግራይ ማዕከላዊ ዞን መረብ ለኸ ወረዳ የራማ ከተማ ነጋዴ ወይዘሮ ርግአት አባይ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የመንገዱ ግንባታ መጓተት ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
"መንገዱ እጅግ አቧራ ነው ፣ ሁለት ዓመት ሙሉ በዚሁ ስንመላለስ ለበሽታ ተዳርገናል" ብለዋል።
በሶስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ በ2010 ዓ.ም. ግንባታው ሲጀመር የሰሙ ቢሆንም እስካሁን ያለው አፈጻጸም ብዙ እንደሚቀረው ታዝበዋል።
"በቀረው አንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል የሚል እምነት የለኝም "ያሉት ወይዘሮዋ ፣ የሚመለከታቸው አካላት ግንባታውን ማፋጠን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የህዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪ አቶ ታዲስ በርሃነ በበኩላቸው፣ የመንገዱ ግንባታ መጓተቱ በስራቸው ላይ ችግር ከመፈጠሩ ባለፈ መኪናቸው ለብልሽት እየተዳረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ግንባታው ከተጀመረ ሁለት ዓመት እንደሆነውና እስካሁን የአስፋልት ንጣፍ ሰራው እንዳልተጀመረ አመልክተው በመንገዱ ግንባታ መጓተቱ ቅር መሰኘታቸውን ገልጸዋል።
በግንባታ ላይ ያለው መንገድ በመቆፋፈሩ በአቧራ ለተሽከርካሪም ለእግረኛም አስቸጋር እንደሆነ አስረድተዋል።
ተለዋጭ መንገድ ስለሌለው የህዝብ ማመላለሻና የግንባታ ስራ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መንገዱን እያጨናነቁት እንደሆነ እና በጊዜ ገደቡ ተጠናቆ ለአገልገሎት እንዲበቃ ከወዲሁ ትኩረት እንዲሰጠው ጠቁመዋል።
"መንገዱ ለአደጋ አጋላጭ በመሆኑ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማገኘት ግንባታው ማፋጠን ይገባል "ያሉት ደግሞ በዓድዋ ወረዳ የዓዲ በሪኽ አካባቢ ነዋሪ አቶ ግርማይ አበራ ናቸው።
በተቋራጭነት መንገዱን የሚሰራው ድርጅት የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመንፈስ ኪዳነ በበኩላቸው 40 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገዱ ግንባታ አሁን ላይ 37 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
የመንገዱ ግንባታ በወሰን ማሰከበር እና ገደላማ ተፈጥሮዊ አቀማመጥ ምክንያት መጓተት ቢኖርም አስቸጋሪ የነበረው የአፈር ቆረጣ ፣ ሙሌትና የቱቦዎች ቀበራ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
''አስቸጋሪ የሚባለው ስራ ተሰርተዋል፣ካሁን በኋላ የሚቀረው ቀላል ስራ ነው፣የአስፋልት ንጣፍ ስራው በመጪው የካቲት ወር ይጀምራል'' ብለዋል።
ስራ እስኪያጁ እንዳሉት ደረጃውን ጠብቆ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው።
የመንገዱ ግንባታ ፕሮጀክት ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለው አፈጻጸም ድክመት እንደነበረበት ከተገመገመ በኋላ መሻሻል ማሳየቱን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ናቸው።
ተቋራጩ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲያጠናቅቅ ባለስልጣኑ ክትትልና ድጋፉን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።
በሶስት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ ታህሳስ 2010 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የዓድዋ ራማ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ለኢትዮ- ኤርትራ ግንኙነት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ታምኖበት የፌዴራል መንግስት በመደበው 807 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄድ እንደሆነ ተመልክቷል።