ቀጥታ፡

በ2019 የንግድ አውሮፕላኖች ባጋጠማቸው አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ50 በመቶ በላይ ቀንሷል

ኢዜአ፤ታህሳስ 23/2012 በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2019 ግዙፍ የንግድ አውሮፕላኖች ባጋጠማቸው የመከስከስ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ50 በመቶ በላይ መቀነሱን አንድ የበረራ ኢንዱስትሪ የዳሰሳ ሪፖርት ጠቁሟል።

ባለፈው ዓመት በተከሰቱ አደጋዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 257 ሲሆን በ2018 ደግሞ 534 ነበር ሲል የበረራ ጥናትና ማማከር ላይ የሚሰራው To70 የተሰኘው ድርጅት ጠቅሷል።

ሆኖም በመጋቢት ወር ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወታቸው ያለፈበት አሳዛኝ ዓመት እንደነበርም ነው የገለጸው።

በ2019 ግዙፍ የንግድ አውሮፕላኖች በረራን ጨምሮ 86 የመከስከስ አደጋዎች ያጋጠሙ ሲሆን በስምንቱ አደጋዎች በአጠቃላይ የ257 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ይህም ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ሲጓዝ ተከስክሶ የ157 ሰዎች ህይወት ያላፈበትን አደጋም ይጨምራል።

በዳሰሳ ጥናቱ መሰረት ከ5.58 ሚሊዮን ግዙፍ የመንገደኞች አውሮፕላን በረራዎች ውስጥ በአማካይ በአንዱ የሞት አደጋ ተመዝግቧል።

በፈረንጆቹ 2018 መቶ ስልሳ አደጋዎች የደረሱ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በ13ቱ አደጋዎች የ534 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የበረራ ደህንነት ዳሰሳ የሚያደርገው የአቪየሽን ሴፍቲ ኔትወርክ በድረገፁ ባስቀጠመው መረጃ መሰረት ያለፈው 2019 ዓመት ለንግድ የአውሮፕላን በረራዎች ጥሩ የሚባል ዓመት ነበር።

በዓለም የበረራ ኢንዱስትሪ  ውስጥ ድህንነቱ  የተጠበቀ ጉዞ በአማካይ የተመዘገበበት ዓመት 2017 ነው።

በዚያ ዓመት የመንገደኞች ህይወት ያለፈበት ግዙፍ የንግድ አውሮፕላን አደጋ አላጋጠመም።

ጥናቱ በአነስተኛ አውሮፕላኖች፣ በወታደራዊ አውሮፕላን በረራዎች፣ በስልጠና በረራዎች በግል እና በዕቃ ማጓጓዣ አውሮፕላኖች እና በሄሊኮፕተሮች ስለደረሰው አደጋ በዳሰሳ አለማካተቱን ገልጿል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም