መልካም እሴቶቻችንን በማሳደግና የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላም በመፍታት ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል - የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
መልካም እሴቶቻችንን በማሳደግና የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላም በመፍታት ሃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል - የሃይማኖት አባቶች
ኢዜአ ታህሳስ 22/2012 መልካም እሴቶችንን በማሳደግና የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላም በመፍታት ሁሉም ዜጋ ለህዝብና ለሃገር አብሮ በመቆም ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አስተላለፉ። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ የዕምነት ተቋማት መሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የፓናል ውይይት ዛሬ አካሂዷል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የብፁዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ልዩ ፅህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ፣የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሰላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሸኽ መሃመድ ሲራጅ ኡመር እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃድቁ አብዱ በውይይቱ ተሳትፈዋል። በውይይቱ ላይም በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየተስተዋለ የመጣው የሰላም ችግርና ወደፊት መወሰድ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ የእምነት ተቋማት መሪዎቹ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል። በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተማሪዎች መካከል የሚፈጠረው ግጭት፣ መጪውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ “ምን መደረግ አለበት?” የሚሉት ነጥቦች የውይይቱ ዋና ሀሳቦች ናቸው። ኢትዮጵያዊያን አብሮ የመኖር፣ የመተሳሰብና የመቻቻል የበለጸገ የመልካም እሴቶች መገለጫ ባህል አላቸው። እነዚህ ለዘመናት የቆዩት መልካም እሴቶቻቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ለምን ተሸረሸሩ? የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ተሰሚነት እየቀነሰ የመጣው ለምንድን ነው? ለሃይማኖት ተቋማት መሪዎቹ የቀረቡ ጥያቄዎች ናቸው። ሃይማኖት መሪዎቹ በአሁኑ ወቅት የመልካም እሴቶቹ መሸርሸር እና በአሁኑ ወቅት ለመስተዋሉት ችግሮች ምንጭ የሆኑትን ጉዳዮች በሶስት ይከፈላሉ። ለዚህም በቀዳሚነት የሚያነሱት የግል ፍላጎት ያላቸው አካላት ህዝቡን ከሃይማኖቱ የመነጠል፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ትልልቅ ሰዎች እንዳይሰሙና ቦታ እንዳይኖራቸው የማጥላላት ዘመቻ እየተካሄደ መምጣቱ ነው። በተጨማሪም የእምነት መፅሃፍትን ቃላት ከአውድ ውጭ በመተርጎምና በፖለቲካ ውስጥ በመጠቀም የዕምነቱ እውቀት ክፍተት በሚታይበት አካባቢ መቀስቀሻ መሳሪያ በማድረግና ግጭት ለመፍጠሪያነት በመጠቀማቸውም መሆኑን ይጠቅሳሉ። ከሃይማኖት አባቶቹ ከራሳቸው አውቀው ወይም ሳያውቁ የሚወጡ የተሳሳቱ መረጃዎች፣ በየቤተ እምነቱ አንዱን ከአንዱ ሃይማኖት ጋር የሚያቃርኑ ሰበካዎች መካሄዳቸውን በሶስተኛ ምክንያትነት አውስተውታል። የሃይማኖት አባቶች እነዚህን ሀሳቦች ከግምት ውስጥ በማስገባት የራሳቸውን እምነት ሲያስተምሩ የሌላውን እምነት በማይነካ መልኩ መሆን እንዳለበት ነው የእምነት ተቋማት መሪዎቹ የተናገሩት። ሁሉም በአጽንኦት የገለጹት ነጥብ 'ከምንም በላይ አብሮነት፣ አገርንና ሰላምን ማስቀድም' አስፈላጊነት ላይ ነው። ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ "እነዚህ ቦታዎች የእግዚያብሄር ቦታዎች ተብለው ተለይተዋል፣የማንም አይደሉም ቤተ እምነቶች ናቸው ስረአተ አምልዕኮ የሚፈፀምባቸው ቦታዎች ናቸው እና ሊከበሩ ይገባል እንደዚህ አይነት ተግባር ሲፈፀሙ ደግሞ የሃይማኖት ሰዎች ረጋ ብለው አስታውለው ወደነበረው አብሮ የመኖር ስሜት መመለስ ደግሞ ብልህነትና ማስተዋል ነው" ብለዋል። "እኔ በዕምነቴ ስም አንድ መጥፎ ነገር ከሰራሁ መጨረሻ የሚጎዳው የኔ እምነት ነው መክንያቱም መጥፎ ነገር ከሰራሁ በዛ እምነት ስም ሰው ይሄንን ነው እንዴ የሚያስተምረው ይሄ እምነት ብሎ እምነቱን ወደ መጥላት ስለሚሄድ ሃይማኖትን እና የዕምነት ቦታዎችን መንም አይነት መግለጫ ሰጥቶ ፣በምንም ማብራሪያ ምክንያት መድፈር ከዚህም አልፎ ማቃጠል፣ማፍረስ በጣም ፅዩፍና ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው"በማለትም ገልጸዋል ጳጳሱ ። ሸኽ መሃመድ ሲራጅ ኡመር " እውነቱን ካወራን እውነቱን ከሰራን ከህዝብም ከሃይማኖት አባቶችም የሚደበቅ ነገር የለም ።እኔና አባቴ ጎን ለጎን ነው የተቀመጥነው ይህ አቀማመጥ ዟሂር ብቻ በላይ የሚታይ አቀማመጥ መሆን የለበትም ውስጣችንም የተቀራረበና እምንተዛዘን መሆን አለብን። " ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተማሪዎች መካከል የሚስተዋለው ግጭት የእምነት አባቶቹ በቁጭት የገለጹት ነጥብ ነው። ለዚህ እንደምክንያት ያነሱት በውጭ ማህበረሰብ የሚታዩ ግጭቶችን፣ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችንና ያለፉ መጥፎ ታሪኮችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በማስገባት ግጭት ለመፍጠር ተግባር እየዋለ መሆኑን ነው። የእውቀት ምንጭና የነገ አገር ግንባታ መሰረት የሆኑትን የትምህርት ተቋማት የግለሰቦችና ቡድኖች አጀንዳ ማስፈፀሚያና የግጭት ማዕከል በማድረግ የመጠቀም አዝማሚያን በመከላከል ሁሉም ዜጋ የራሱን ሃላፊነት መወጣት እንደሚጠበቅበት የሃይማኖት መሪዎቹ አንስተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ "በዩኒቨርስቲዎችም በተለያዩ ቦታዎችም የሚታዩ አለመግባባቶች ግጭቶች ሁሉ ያልፋል ነገሩ የሆነው ሆኖ ግን ጥሎት የሚያልፈው ነገር ጥሩ ያልሆነ አሻራ ስለሆነ ለምን እንደገና ለቀጣዩ ትውልድ የቤት ስራ እናስቀምጣለን፣ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ ለምን አንፈታም ለቀጣይ ትውልድስ ለምን አናስብለትም" ፓስተር ፃድቁ አብዱ "ባልንጀራን እንደራስ መውደድ ማለት የኔ ብሄር ነው ፣የኔን ብሄር አባልም የኔን እምነት ተከታይም መሆን የለበትም ሰው በመሆኑ ብቻ ለሰው ክብር መስጠት ከብር ለሚገባው ክብር መስጠት የሚለውንም ሃሳብ እዚህ ውስጥ ማዬት ያስፈልጋል ብለዋል። ሸኽ መሃመድ ሲራጅ ኡመር "እውነት ለሃቅ የቆምን ከሆንን፣እውነት የእውነት የሃይማኖት አባቶች ከሆንን ሰዎች ሲደማሙ ሲቆሳሰሉ፣ሲፈናቀሉ ማዬት ያስለቅሰናል፣ያሳዝነናል በተለይ የዕምነት አባቶች እዚህ ላይ ከውስጥ በደንብ መስራት አለበን''በማለትም ጠቁመዋል። የመጪውን ምርጫ ዝቅጅትን ጨምሮ አጠቃላይ ሂደት ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ገለልተኛ ለማድረግ የሚያስችል ድባብ ለመፍጠር ከእያንዳዱ አካል ምን እንደሚጠበቅም ለሃይማኖት ተቋማቱ መሪዎች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። በአገሪቷ ውስጥ ለሚከናወኑ ማናቸውም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ መስተጋብሮች የአገር ሰላም ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው መሆኑን የሃይማኖት መሪዎቹ ተናግረዋል። በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ቅስቀሳ ሰዓታቸው ጀምሮ በሰላምና አብሮ በመኖር ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውም ነው መሪዎቹ ያሳሰቡት። ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ "ሰላምን ማስቀደም አለብን በዬ ክልሉም፣በየዞኑም፣በየ ወረዳውም ቢሆን ለሃገር እሚበጀውን ለሀዝብ የሚጠቅመውን ነገር አቅርበው ሀዝቡ እንዲቀበላቸው ማድረግ ነው እንጂ በሃይል በጉልበት የነበረውን ስህተት ዛሬ ላይ መድገም የለብንም " ሸኽ መሃመድ ሲራጅ ኡመር "ፍትህ አለ ግን ፍትህ የሚያዛቡ አካላት ደሞ አሉ ሀዝብ ውስጥ አሉ ፣እምነት አባቶች ውስጥ አሉ ፣አስተማሪዎች ወስጥ አሉ እነዚያ ማቆም አለባቸው ፣መተው አለባቸው" ይላሉ። ፓስተር ፃድቁ አብዱ እንዳሉት"አገር ሰላም ሲኖር ስለሆነ መምራት የሚቻለው በመጀመሪያ ደረጃ የአገር ሰላም እንዲረጋገጥ እምንችለው ከሁሉ በላይ ትልቁ ነገር እኛ ማድረግ እምንችለው ፀሎት ነው እሱን እናደርጋለን ፣ሌላው ደግሞ በየቤተ እምነቱም ያለው ምዕምን ተረጋግቶ ካርድ ስለሆነ መጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት በህሊናው ትክክል ነው ብሎ ላመነው አካል ድምጽ እንዲሰጥ ያስፈልጋል ።" ከምርጫ በኋላም ምርጫውን ያሸነፈው አካል ለመረጠውም ላልመረጠውም እኩል ማገልገል፣ ያልተመረጠው ደግሞ ከስህተቱና ከህዝቡ ፍላጎት ተነስቶ ለቀጣይ ሰላማዊ ምርጫ እራሱን ማዘጋጀት እንጂ ከግጭት ትርፍ ለማግኘት መፈለግ የለበትም ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።