ቀጥታ፡

በግጭት የሚደርሰውን የንፁሀን ደም መፍሰስ ለማስቆም የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች ተስማሙ

ኢዜአ ታህሳስ 22 ቀን 2012 በአፋርና ሶማሌ ህዝብ መካከል በሚከሰት ግጭት የሚደርሰውን የንፁሀን ደም መፍሰስ ለማስቆም የሁለቱ ክልል የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች ተስማሙ። በኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት አማካይነት በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የምክክር መድረክ ግጭቶችን ለማስቆም ባለ 8 ነጥብ የጋራ አቋም መግለጫ በማውጣት ዛሬ ተጠናቋል። በመድረኩ ላይ የሶማሌ ክልል ገራድ ኩልሚዬ ገራድ ሙሀመድ የመድረኩ ተሳታፊዎች በህዝቦች መካከል በሚፈጠር ግጭት የሚከሰተውን የንፁሀን ደም መፍሰስ ለማስቆም በጋራ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል። የአፋርና የሶማሌ ህዝብ በሃይማኖት አንድ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከአንድ የዘር ሐረግ መፈጠራቸውን የገለጹት ገራድ ኩልሚዬ፣ "በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት የሚነሳበት ምክንያት በሃይማኖትም ሆነ በባህል ተገቢነት የሌለውና የሚወገዝ ነው" ብለዋል። በእዚህም የሁለቱ ክልል የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች የተፈጠረውን አለመግባባትና ግጭቶችን ለማስቆም ቃል ገብተው መስማማታቸውን ተናግረዋል። ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው በአገር ሽማግሌዎች የተቀመጠውን አቅጣጫ እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ድረስ ለማውረድ በሙሉ አቅማቸው እንደሚሰሩ አመልክተዋል። "በአፋር እና ሶማሌ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች በሙሉ እምነት ተቀብለን ለመተግበር እንሰራለን" ያሉት ደግሞ ሱልጣን አንፊሬ አሊሚራህ ናቸው። ሁለቱ ህዝቦች ከልዩነታቸው ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው ጉዳዮች ሰፊ መሰረት እንዳላቸው ጠቁመው፣ "በመካከላቸው የተከሰቱ ግጭቶች በመሰረታዊነት እንዲፈቱና አካባቢው ወደቀደመው ሰላም እንዲመለስ ከሁለቱም ህዝቦች ጋር በትብብር ለመስራት ቃል ገብተናል" ብለዋል። ሰላም ለሁሉም ወሳኝ በመሆኑ ችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ በሙሉ እምነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል። "ለልማትና እድገት፣ ለአገራዊ አንድነት ሰላም ቀዳሚ ነው" ያሉት ሱልጣን አንፊሬ፣ "በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና በሁለቱ ህዝቦች መካከል እርቀ ሰላም ለማውረድ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ነጥቦች በሙሉ አክብረን ለተግባራዊነታቸው እንሰራለን"  ብለዋል። የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ሰብሳቢ አባገዳ በየነ ሰንበቶ በበኩላቸው በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የጎሳ መሪዎች፣ ዑጋዞችና የአገር ሽማግሌዎች በውይይትና በመነጋገር እንዲፈቱ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። ይህም ህብረተሰቡ ወደሰላማዊ ህይውቱ እንዲመለስ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና እርቀ ሰላም በአካባቢው ለማውረድ መልካም ጅማሮ መሆኑን ነው የገለጹት። የሁለቱ ብሔር መሪዎች መገዳደልና ደም መፋሰስ እንዲያቆሙ ስምምነት ላይ መደረሱንና ተግባራዊነቱን በጋራ እንዲከታተሉ ጭምር አቅጣጫ መቀመጡንም አባገዳ አስረድተዋል። በእዚህም ከሁለቱ ክልል የተወከሉ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎች ከሶማሌና አፋር ክልል መንግስታት እንዲሁም ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን በአካባቢው ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ በቅንጅት እንደሚሰራ አመልክተዋል። በአካባቢው የግጭት መንስኤ የሚሆኑትን ለይቶ ከመንግስት የአስተዳደር አካላት፣ ከየጎሳ መሪዎችና ማህበረሰብ ጋር በትብብር የመፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ እንዲሰራም አመልክተዋል። አባገዳ በየነ እንዳሉት ከግጭቶች ጋር ተያይዞ በአካባቢው ጥፋት ሳይገኝባቸው የታሰሩ አካላት ካሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ እንዲፈቱ፣ አዳዲስ ሰፈራዎች በሁለቱም የክልሉ አካባቢዎች እንዲቆሙ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ከእዚህ በተጨማሪ ህዝቡን የሚያጋጩ አሉባልታዎች እንዲቆሙና ችግር ሲከሰትም ፈጣን እልባት ለመስጠት የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተገናኝታው እንዲወያዩ አቅጣጫ መቀመጡን አባገዳ በየነ አስረድተዋል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም