ሥርዓተ ፆታን ያገናዘበ የመገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ መመሪያ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ሥርዓተ ፆታን ያገናዘበ የመገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ መመሪያ ተዘጋጀ
ኢዜአ ታህሳስ 22/2012 ሥርዓተ ፆታን ያገናዘበ የመገናኛ ብዙሃን አዘጋገብ መመሪያ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ። በመመሪያው ዙሪያ ለህትመት ፣ ቴሌቭዥንና ሬዲዮ ጋዜጠኞች የተዘጋጀ የሶስት ቀናት ሥልጠና መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ በዚህ ወቅት እንዳሉት መመሪያው የተዘጋጀው ከ"ዩ ኤን ውመን " ጋር በመተባበር ነው። "መመሪያው መገናኛ ብዙሃን ስለ ሥርዓተ ፆታ የተሻለ አረዳድ ኖርዋቸው የሴቶችንና ወንዶችን ሰብአዊ መብት ለማጉላት ያስችላል "ብለዋል። በተለይ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት፣ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና አመራር ሰጪነት ለማሳደግ የሚኖራቸውን ሚና ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል። መመሪያውን በማዘጋጀት ሂደት በተለያዩ የህትመት፣ ቴሌቭዥና ሬዲዮ አማካኝነት የተላለፉ ናሙናዎች ተዳሰዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በተለያዩ ዓለም ፣አህጉር እና ሀገር አቀፍ ደረጃ የወጡ የሕግና የፖሊሲ ሰነዶችንም ለመቃኘት ተሞክሯል። የመመሪያው አጠቃቀም በመልዕክት ቀረፃና በይዘት ቅንብር፣በቃለ መጠይቅ፣በዜና ዝግጅት፣ሥዕላዊ መግለጫዎችን ጨምሮ የአርትኦት ሥራ ሲከናወን ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በ "ዩ ኤን ውመን" የኢትዮጵያ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ የልፍኝ አበጋዝ በበኩላቸው ከባለስልጣኑ ጋር በመተባበር መገናኛ ብዙሃን የፆታ እኩልነትና የሴቶች አመራር ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ፕሮግራም ቀርጸው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸዋል። በፕሮግራሙ የመገናኛ ብዙሃን ስርዓተ ፆታን ያገናዘበ አሰራርና መዋቅር እንዲኖራቸው ለማስቻል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በዚህ ዙሪያ መመሪያ ተዘጋጅቶና ታትሞ ለመገናኛ ብዙሃን አካላትና ባለሙያዎች በማሰራጨት ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሰራ ነው። በአሁኑ ወቅትም ስርዓተ ፆታን ያገናዘበ የማስታወቂያ ስርጭትን ለመምራት የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስተባበሪዋ ጠቁመዋል።