ቀጥታ፡

ባህላዊና ዘመናዊ የግጭት አፈታት ዘዴን አግባብቶ መስራት ለውጤታማነት እንደሚያበቃ የህግ ምሁራን ገለጹ

ኢዜአ ታህሳስ 22/2012 ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ባህላዊና ዘመናዊ የግጭት አፈታት ዘዴን አግባብቶ መስራት ለውጤታማነት እንደሚያበቃ የህግ ምሁራን ገለጹ።

"የቆዩ ባህላዊ እሴቶች ለግጭት አፈታት ያላቸው ጠቀሜታ" በሚል ርዕስ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲና በኦሮሚያ የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የተዘጋጁት የምክክር መድረክ በፍቼ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በሰላሌ ዩኒቨርስቲ የህግ ፋክሊቲ ዲን አቶ ዘላለም ተስፋዬ  እንዳሉት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ባህላዊና ዘመናዊ የግጭት አፈታት ስልቶችን ማናበብ ፣ማግባባትና ማስማማት ያስፈልጋል  ።

"በተለይ የቆዩ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስራዎች ለዘመናዊ የፍትህ ስራ ትልቅ ግብኣት እንዳላቸው ሁሉ የራሳቸው የሆኑ ጉድለቶችን ለማቻቻል ብሎም ለማረም መናበብ ወሳኝነት ያለው ነው "ብለዋል ።

በሀገሪቱ ለፍትህ ስራ አንጋፋ የሆኑ ባህላዊ እሴቶች እንዳሉ ጠቁመው በተለይ በገዳ ስርዓት ውስጥ ያለው የጉማ የእርቅና የካሳ ስርዓት ለዘመናዊ የፍትህ ሥርዓት ትልቅ ግብአት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

"ስርዓቱ  በዘመናዊ ፍርድ ቤቶች የሚፈጠረውን የጊዜ ፣የጉልበትና የገንዘብ ብክነት በማስቀረት ህብረተሰቡ ተቻችሎ በሰላምና በአብሮነት  እንዲኖር የሚያደርግ በመሆኑ ሊጠናከር ይገባዋል "ብለዋል ።

ይህ የግጭት አፈታት ስርዓት ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሚቻልበትን ሃገር በቀል  ዘዴ  እንዳለ በጽሁፋቸው አመላክተዋል።

የዞኑ  ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት አቶ እሸቱ ያደታ በበኩላቸው መሰረታዊ ባልሆኑና በጥቃቅን ግጭቶች የተነሳ የህዝቦች አንድነትና ልማት እንዳይስተጓጐል የሚያስችሉ ጥናቶችን በየጊዜው በማድረግ ለህብረተሰቡና ለሀገር ሽማግሌዎች ትምህርት  መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስወገድ የኃይማኖት ተቋማት፣የሀገር ሽማግሌዎችና ልዩ ልዩ ማህበራት እርስ በርሳቸው የልምድ ልውውጥ እንዲያሰርጉ ማመቻት ይገባል።

በዚህም አንዱ ከሌላው በመማር  የሚያጋጥሙ ግጭቶችን ቀድሞ በማጥናት ማስወገድ እንዲቻል አዳዲስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መጀመራቸውንም የፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት አመልክተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ አባገዳ መኮንን በዳኔ አብዛኛውን ጊዜ የግጭት መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶች አነስተኛ ግምት የሚሰጣቸው ቢሆኑም መዘዛቸውን ከወዲሁ በመረዳት እልባት ለመስጠት ግንዛቤ መፍጠሩ  ወሳኝነት እንዳለው ተናግረዋል።

የእምነት አባቶችም ሆኑ የሃገር ሽማግሌዎች የቆዩ ባህላዊ እሴቶችን መሰረት በማድረግ ለቃልና ተግባራቸው ታማኝ በመሆን ህብረተሰባዊ ችግሮችን በኃላፊነት ስሜት መዳኘት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

በተለይ የእምነት፣ የብሄርና የጐሣ መሰረት ያደረጉ ትንኮሳና ግጭቶች መፈታት ያለባቸው በባህላዊ የእርቅና የካሣ ስርዓት  መሰረት አድርገው መሆን እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

"በፍትህ ስርዓት ውስጥ የሀገር ሽማግሌዎችና የእምነት አባቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ በእውቀትና በትክክለኛው ባህላዊ መንገድ ሽምግልናቸውን ማካሄድ ይጠበቅባቸዋል" ያሉት ደግሞ የግራር ጃርሶ ወረዳ ፍርድ ቤት የህግ ባለሙያ  አቶ ሸዋረጌ እሸቱ ናቸው።

የዞኑ አስተዳደር የህዝብ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኮንን ይልማ የለውጥ ሂደቱን ተከትሎ ግጭቶችን ለማባባስ የሚጥሩ አካላትን  ለመቋቋም ባህላዊ ወግና ስርዓት መጠቀም ተገቢ በመሆኑ ሁሉም ወገን በትብብር መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

በውይይቱ በቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ከመስጠት ባሻገር  ለጋራ ጠቀሜታ በሚውሉ ጉዳዩች መግባባት ላይ ተደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም