ቀጥታ፡

የባዕከር-ዓዲ-ረመፅ አስፓልት መንገድ ግንባታ አፈጻጸም 68 በመቶ ደረሰ

ኢዜአ ታህሳስ 22 ቀን 2012 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን የባዕከር-ዓዲ-ረመፅ የአስፓልት መንገድ ግንባታ አፈጻጸም 68 በመቶ መድረሱን የተቋራጭ ድርጅቱ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የመንገድ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ገደብ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ተቋራጩ የሱር ኮንስትራክሽን መንገድ ፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ አብረሃ ለኢዜአ እንዳሉት  የመንገዱ ግንባታ ጥቅምት 2012 ዓ.ም ነበር የተጀመረው።

የመንገዱ ግንባታ ካለው 70 ኪሎሜትር ውስጥ 17 ኪሎ ሜትሩ አሰፓልት መልበሱን አመልክተዋል።

ቀሪው የመንገዱ ክፍል የአፈርና አለት ቆረጣ፣የአፈር ድልደላና የድልድዮች ግንባታ ስራ እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል ።

አጠቃላይ የግንባታው ደረጃ አፈጻጻም 68 በመቶ ደርሷል።

እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ የመንገዱ ግንባታ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን   ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ በበኩላቸው የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እየተከናወነ መሆኑን  ገልጸዋል።

አሁን ባለው የግንባታ ሂደት ስራው በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

በቃፍታ ሁመራ ወረዳ የዓዲ ሕርዲ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሄለን እንኮየነ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው ከተሞችን የሚያገናኝ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለመኖሩ በንግድ ስራ ከሚተዳደርበት ዓዲ ሕርዲ ከተማ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

“የንግድ እቃዎችን ለማመላለስ እቸገር ስለነበር መኖሪያ ቤቴን ትቼ ወደ ባዕከር ከተማ ለመምጣት ተገድጃለሁ” ብለዋል።

መንገዱ  በአስፓልት ደረጃ መገንባቱ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው   በመመለስ  ለመነገድ  ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው አመላክተዋል ።

"ከተሞችን በትራንስፖርት የሚገኛኝ አመቺ መንገድ ባለመኖሩ ወደ ባዕከርና ዓዲ ረመጽ ከተሞች በእግር በመጓዝ የሰሊጥና ማሽላ ምርታችንን ለመሸጥ ስንገደድ ቆይተናል” ያሉት ደግሞ የዓዲ-ሕርዲ ከተማ ነዋሪ አቶ ዘውዱ አስማረ ናቸው።

የመንገዱ ግንባታ አስፓልት መሆኑ ምርታቸውን በትራንሰፖርት በማጓጓዝ አማራጭ በሚሉት ገበያ በቀላሉ ለመሸጥ እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም