ቀጥታ፡

የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር ተጀምሯል

ኢዜአ ታህሳስ 22/2012 የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ተጀምሯል። በውድድሩ መክፈቻ ቀን በተደረጉ ጨዋታዎች ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል። ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው። የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ውድድሩ የተዘጋጀው ክለቦች ፕሪሚየር ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ያሉበትን ደረጃ እንዲፈትሹ ነው። ዘንድሮ የተቋቋሙት ብሔራዊ አልኮል አረቄ ፋብሪካ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሴት ቮሊቦል ክለቦች መነቃቃትን እንደሚፈጥሩ ገልጸው፤ ሌሎችም ክለብ በማቋቋም ለስፖርት እድገት እንዲሰሩ ጠይቀዋል። የሴቶች የቪሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የውድድር አማራጭ በማስፋት በተያዘው ዓመት የጥሎ ማለፍ ውድድርና አገር አቀፍ ሻምፒዮና እንደሚካሄድም ጠቁመዋል። የሐበሻ ሲሚንቶ የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የአቋም መለኪያ ውድድር ዛሬ ሲጀመር ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል። በውድድሩ የመጀመሪያ ጨዋታ ፌደራል ማረሚያ ቤቶች በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጌታዘሩ ስፖርት ክለብን 3 ለ 1 አሸንፏል። ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በመጀመሪያ ዙር ቢሸነፍም ያለውን ልምድ ተጠቅሞ ተከታታይ ሶስት ዙሮችን በማሸነፍ የጨዋታው አሸናፊ ሆኗል። ጌታዘሩ ስፖርት ክለብ የመጀመሪያውን ዙር ሲያሸነፍ ያሳየው ጥሩ ብቃት በቀጣዮቹ ዙሮች እየተዳከመ የመጣ ሲሆን የአሰራረብ ስህተትና የቦታ አያያዝ በቡድኑ ላይ የታዩ ድክመቶች ናቸው። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አሰልጣኝ ምክትል ኮማንደር ጫልቺሳ ደፋ በጨዋታው ቡድናቸው በማሸነፉ ቢደሰቱም በአሰራረብና የጨዋታ ዝግጁነት ላይ የታዩ ክፍተቶች ማረም እንዳለባቸው ማየት መቻላቸውን ገልጸዋል። የጌታዘሩ ስፖርት ክለብ አሰልጣኝ ሰልማን ኢብራሂም በበኩላቸው የቅንጅትና የጨዋታ ዝግጁነት ሰፊ ክፍተት እንደነበረባቸውና በቀጣይ እንደሚያርሙት አመልክተዋል። በሁለተኛ ጨዋታ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች የሰበሰበው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በታዳጊ ወጣቶች የተደራጀውን ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን 3 ለ 0 አሸንፏል። የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ አሰልጣኝ ሽመልስ መገርሳ በጨዋታው ቡድናቸው በአሰራረብና ቦታ አያያዝ የተወሰኑ ክፍተቶች እንዳዩና በቀጣይ ጨዋታ ይሄን አርመው እንደሚቀርቡ ገልጸዋል። የወላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ አሰልጣኝ ትዕግስቱ ጉተና ክለቡ አዲስ እንደመሆኑ ውድድሩን ለልምድ መቅሰሚያ እንደሚጠቀምበት ተናግረዋል። ለሴቶች የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የውድድር አማራጭን ማስፋትና ክለቦቹ በዓመት ውስጥ የሚያደርጉትን የጨዋታ ቁጥር ማሳደግ ሌላኛው የውድድሩ አላማ እንደሆነ ተናግረዋል። ''የተዳከመውን የሴቶች ቮሊቦል የስፖርት እንቅስቃሴ ለማነቃቃትም የውድድሩ መዘጋጀት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል'' ብለዋል። በሴቶች ቮሊቦል ለረጅም ጊዜ የቆዩ ተጫዋቾች ተተኪ አለማግኘታቸውና ክለቦች በግለሰቦች ፈቃድ መቋቋምና መፍረስ የሴቶች ቪቦል ስፖርት እንቅስቃሴ እንዲዳከም እደዳደረገው አመልክተዋል። የተተኪ ተጫዋቾችን አለመፍራት የቮሊቦል ታዳጊ ፕሮጀክቶች በአመላመልና ስልጠና ውጤታማ ባለመሆኑ እንደሆነ ነው አቶ ተክሉ ያስረዱት። በወንዶችም በሴቶችም ውጤታማ ያልሆነውን የስፖርቱን የታዳጊ ፕሮጀክት ማጠናከርና ስፖርቱ እምቅ ችሎታ ያለባቸውን ቦታዎች ለይቶ የመስራት ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል። በአፍሪካ መድረኮች ኢትዮጵያን ወክሎ ውጤታማ የሆነው አንጋፋው ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ባለፈው ዓመት መፍረሱን አስታውሰው የክለቦች መፍረስ የስፖርቱ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል። ''በመሆኑም ክለቦች ሲፈርሱ ተጠያቂ ሊሆኑበት የሚገባ የአሰራር ስርአት መዘርጋት ያስፈልጋል'' ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም