ቀጥታ፡

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተግዳሮቶችና የወደፊት ልማት ላይ የሚመክር አገር አቀፍ ኮንፈረንስ ሊካሄድ ነው

ታህሳስ 22/2012 በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመለየትና የዘርፉን ልማት ማፋጠን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚመክር አገር አቀፍ የንቅናቄ ኮንፈረንስ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በኮንፈረነሱ ላይ የኢንዱስትሪው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ይፋ ይደረጋል ተብሏል። ኮንፈረንሱን በተመለከተ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እንዲሁም የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም መዘግየትን ፣  ከጨረታ ውጭ ተጨማሪ ክፍያን በመጠየቅ ለኪሳራ መዳረግን ጨምሮ አያሌ የህግ ፣ የአሰራርና የአቅም ችግሮች እንዳሉበት በዚሁ ወቅት ተመልክቷል። አገር አቀፍ የንቅናቄ ኮንፈረንሱ የተዘጋጀውም ለዘርፉ አፈፃፀም እንቅፋት የሚሆኑትን እነዚህን ችግሮች ጨምሮ  አጠቃላይ ተግዳሮቶችን ለመለየትና መፍትሄ ለመዘየድ መሆኑን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሊድ አብድረህማን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አስመሮም ታደሰ በበኩላቸው አጠቃላይ የአገሪቱን የኮንስትራክሽን ልማት ለመምራት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ከንቅናቄ ኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ግብዓት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል። በፕሮጀክቶች አስተዳደር ላይ የሚታዩ መዘግየቶችን ለማስቀረት የሚረዱ የአሰራር ስርዓቶች በኮንፈረንሱ ይፋ የሚደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል። በኢንዱስትሪው የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት በኮንስትራክሽን እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋንያንን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በንቅናቄ ኮንፈረንሱ ላይ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ሥራ አመራር ስርዓትም ውይይት ይደረግበታል ብለዋል። ኮንስትራክሽን ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ በዘርፉ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ ናቸው። በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ከ200 እስከ 300 በመቶ የአፈጻጸም መዘግየት የሚታይባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል። ከዚህም ሌላ ከ150 እስከ 200 በመቶ የሚሆኑት ፕሮጀክቶች ከጨረታ ውጭ ተጨማሪ ክፍያ የሚጠየቅባቸው እንደሆኑም በጥናት መረጋገጡት አቶ ማተቤ አብራርተዋል። የህግ ክፍተት ያለባቸው ፕሮጀክቶች እንዳሉም ባለስለጣኑ ባካሄደው ጥናት መረጋገጡን አክለዋል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በኢንዱስትሪው ጤናማነት እና በግብዓት አቅርቦት ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ነገ ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓም በተባበሩት መንግስታት አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የሚካሄደው አገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ንቅናቄ ኮንፈረንስ ለሁለት ቀናት ይቆያል። በኮንፈረንሱ ላይ የኢንዱስትሪው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ይቀርባል የተባለ ሲሆን በአገር ውስጥ የሚመረቱ የተለዩ ስትራቴጂክ የግንባታ ግብዓት አምራች ድርጅቶች ያለባቸው ተግዳሮቶችና ዕድሎች ላይም ኮንፈረንሱ ይመክራል። ከዚህም ሌላ ኮንፈረንሱ የኮንስትራክሽ ኢንዱስትሪው የልህቀት ማዕከል ግንባታ ተልዕኮ ለኮንስትራክሽ ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚሰጠው ጠቀሜታና ያለበት ደረጃን ይገመግማል። ለኮንስትራክሽን ፕሮጀክት የእውቀት መስኮች የሚረዱ 18 ዝርዝር የአሰራር ማኑዋሎች በኮንፈረንሱ ይፋ ይደረጋሉ። በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተሰማሩ አካላትን አቅም በስልጠና በመገንባትና ኢንዱስትሪው በምቹ፣ በጠንካራና በአስተማማኝ የቁጥጥር ስርዓት እንዲመራ ለማድረግ የንቅናቄ ኮንፈረንሱ ጉልህ ሚና እንዳለው ታምኖበታል። በንቅናቄ ኮንፈረንሱ ላይ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር፣ የውኃ ስራ ተቋራጮች ማህበር፣ የሴት ተቋራጮች ማህበር፣ የአማካሪ መሃንዲሶችና አርቴክቶች ማህበር፣ የክልል ስራ ተቋራጮች ማህበር፣ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሚመለከታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት፣ የክልልና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር የዘርፉ አካላት ተሳታፊ ናቸው ተብሎ ይጠበቃል።                                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም