በምስራቅ ወለጋ 45 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ወለጋ 45 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቷል

ኢዜአ ታህሣሥ 22 ቀን 2012 እስካሁን ባለው የበጋ ወቅት 45 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን የምሥራቅ ወለጋ ዞን እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የለማው መሬት በምርት ወቅቱ በእቅድ ከተያዘው 80 ሺህ 476 ሄክታር ውስጥ እንደሆነ ተመልክቷል። በጽህፈት ቤቱ የመስኖ ልማት አግሮኖሚስት አቶ ዋቅጅራ ኤጀርሶ ለኢዜአ እንደገለጹት የመስኖ ልማቱ እየተካሄደ ያለው በዞኑ 17 ወረዳዎች ነው። በዘመናዊ ግድቦች፣ ከወራጅ ወንዝ ውሀ በመሳብና የእጅ ጉድጋዶችን በመጠቀም ልማቱ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ አቶ ዋቅጅራ ገለጻ በቆሎ፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም ፣ ቆስጣ፣ ቀይ ሥር፣ ነጭና ቀይ ሽንኩርት በመስኖ እየለሙ ካሉ ሰብሎችና የጓሮ አትክልቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።ለልማቱ ተሳታፊዎች 5ሺህ ኪሎ ግራም የአትክልት ዘርና 667 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋሉን አስታውቀዋል። የጉደያ ቢላ ወረዳ የወለኔ ሌሙ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ደሣለኝ ቤኛ በሰጡት አስተያየት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ቀይ ሽንኩርት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል ። "ከጓሮ አትክልት ሽያጭ 40 ሺህ ብር ገቢ እጠብቃለሁ" ብለዋል ። በአምስት ሄክታር ማሳ ላይ በቆሎና ድንች እያለሙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የዳርበስ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መልኬ አመንቴ ናቸው። በዞኑ በበጋው ወቅት ከመጀመሪያ ዙር መስኖ ልማት 12 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ታውቋል።