ቀጥታ፡

በዞኑ ከ310 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል ተሰበሰበ

ኢዜአታህሳስ 22 / 2012  በምስራቅ ወለጋ ዞን ከ310 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን  የዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ የአዝርዕት ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ብሩክ ጫላ እንዳስታወቁት በዞኑ ባለፈው የመኸር እርሻ 412ሺህ 668 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። ከእዚህ ውስጥ በ310ሺህ 639 ሄክታር መሬት ለምተው የደረሱ ሰብሎች ተሰብስበዋል፡፡ በዞኑ የደረሱ ሰብሎች የተሰበሰቡት ከመደበኛ የምርት መሰብሰብ ሥራ በተጨማሪ የመንግስት ሠራተኞች፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ተማሪዎችና የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት በዘመቻ ባደረጉት ድጋፍ ነው። ከተሰበሰቡ ሰብሎች መካከል ጤፍ፣ በቆሎ፣ ባቄላ፣ አተር፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ ቦሎቄ እና የመሳሰሉት እንደሚገኙበት የገለጹት አቶ ብሩክ፣ ተሰብስቦ ከተወቃው ሰብል 5 ሚሊዮን 42 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን አመልክተዋል፡፡ አቶ ብሩክ እንዳሉት በአካባቢው ያለወቅቱ መጣል የጀመረው ዝናብ በአሁኑ ጊዜ በማቆሙ አርሶ አደሩ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራ አጠናክሮ ቀጥሏል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዞኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው ያለውን ምቹ የአየር ሁኔታ በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን እየሰበሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከዞኑ አርሶ አደሮች መካከል በዋዩ ቱቃ ወረዳ የቦነያ ሞሎ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብዙነህ ሆርዶፋ እንዳሉት በክረምት ወራት ያለሙትን በቆሎ፣ በርበሬና ኑግ ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመተባበርና የተማሪዎችን ጉልበት በመጠቀም ሰብስበው መከመራቸውን ገልጸዋል፡፡ የወረ ባቦ ሚኛ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገመቹ ያደሳ በበኩላቸው በመኸር እርሻ ያለሟቸውን የተለያዩ ሰብሎች የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ባደረገላቸው ድጋፍ ሰብስበው ማጠናቀቃቸውን አመልክተዋል፡፡ የጤፍና የበቆሎ ሰብሎችን ሰብስበው ማጠናቀቃቸውንና በአሁኑ ወቅትም የዳጉሳ ምርታቸውን በማጨድ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በጉቶ ጊዳ ወረዳ የነጋሣ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ተክሌ ኦሊ ናቸው፡፡ የጉቶ ጊዳ ወረዳ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የልማት ጣቢያ ሠራተኞች ተቆጣጣሪ አቶ ታመነ ያደታ በወረዳው ቆላ አካባቢ የለማ ሰብል ሙሉ በሙሉ፤ በደጋ አካባቢ ደግሞ 70 በመቶ ተሰብሰቦ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ በዋዩ ቱቃ ወረዳ በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው መሬትም 80 በመቶ ያህሉ መሰብሰቡን የገለጹት ደግሞ የወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ የማነ ታደሰ ናቸው ፡፡ በምስራቅ ወለጋ ዞን በ2011/2012 የመኽር ምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው መሬት ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል ፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም