ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሸገር ማስዋብ ፕሮጄክት ሂደትን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሸገር ማስዋብ ፕሮጄክት ሂደትን ጎበኙ
ኢዜአ ታህሳስ 22/2012 በጉብኝቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂአን ተሳትፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ፕሮጀክቱን መስከረም 20-2012 በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት " የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ምንም አይነት ሃይል ሊያስቆመው አይችልም "በማለት መናገራቸው ይታወሳል። በፕሮጀክቱ ከእንጦጦ ተራራ እስከ ባምቢስ ድልድይ ያለው 12 ኪሎ ሜትር ወንዝ እና የወንዝ ዳርቻዎች በመጀመሪያው ዙር የሚለማ መሆኑ ታውቋል። እንዲሁም ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ያለው 42 ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት እንደሚለማም ነው የተገለፀው። ሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት የሚገነባው ግዙፍ ክፍት መዝናኛ እና አደባባይ የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊነት በሚገልፅ መልኩ እንደሚገነባም ነው የተነገረው። በግዙፉ ፓርክ ሰው ሰራሽ ሃይቅ፣ የሰርግ ስነ ስርዓት መከወኛ ስፍራ፣ የሙዚቃ እና የተለያዩ ትርኢቶች መከወኛ ቦታ እንደተካተተ ንድፉ ያሳያል። የህፃናት መጫወቻ፣ የሳይንስ እና ቴክኖሌጂ ማእከልም በፕሮጄክቱ ሁለተኛው ምእራፍ ይገነባሉ ተብሏል። የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምእራፍ ግንባታ በመጪው ግንቦት ወር እንደሚጠናቀቅ የተገለፀ ሲሆን፥ ፕሮጀክቱ የከተማዋን የውበት እና ተፈላጊነትን ይጨምራል። ከእንጦጦ እስከ አቃቂ ለሚሰራው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብ ይፋ በሆነው የ‹‹ሸገር ገበታ›› 255 ሰዎች በባንክ 1 ነጥብ 275 ቢሊዮን ብር ገቢ ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ማስታወቁም አይዘነጋም። ሸገርን ለማስዋብ ከተያዘው የ56 ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት ውስጥ ለሸገር ገበታ 255 ሰዎች እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን ብር ማስገባታቸው መገለጹ ይታወሳል። 56 ኪሎ ሜትር ከሚወስደው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት 14 ኪሎ ሜትር ግንባታው በቻይና መንግሥት የተሸፈነ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ተከታታይ የገቢ ማስገኛ መርሐግብሮች እንደሚቀጥሉም መገለጹ ይታወሳል። ለአጠቃላይ ፕሮጀክቱ 29 ቢሊዮን ብር ስለሚያስፈልግ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የኢትዮጵያ ድርጅቶች እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በይበልጥ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመረው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት ቢሮ ፣ግቢ፣ ከተማና አገር በተባሉ አራት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ቢሯቸውን ማስተካከሉን ጨርሰዋል። በዚህ መሰረትም ቤተመንግሥቱ ለህዝብ ጉብኝት ክፍት ተደርጓል።