ቤተሰቦች ለአባታቸው ተስካር ሊውል የታሰበ 120 ሺህ ብር ለበጎ አድራጊ ድርጅቶች ለገሱ

9

 ኢዜአ ታህሳስ 21/2012  በመቀሌ ከተማ የሚኖሩ ቤተሰቦች ለአባታቸው ተስካር ሊውል የታሰበ  120 ሺህ ብር ለአራት በጎ አድራጊ ድርጅቶች ዛሬ በእርዳታ ለገሱ። የአለቃ ኃይለማርያም ገብረመድህን ቤተሰቦች  ገንዘቡን የለገሱት ለልማትና ለችግረኞች መርጃ እንዲውል እንደሆነ ገልጸዋል።

ቤተሰቦቹ  ለትግራይ ልማት ማህበር፣ ለአባ ፍረሚናጦስ አረጋውያንና ህፃናት ማሳደጊያ ፣ ለሰናይ ተግባር አዕምሮ ህሙማን  እንክብካቤ እና ለሌላ ወላጅ ለሌላቸው ህፃናት ማሳደጊያ ድርጅቶች ለእያንዳንዳቸው 30ሺህ ብር ሰጥተዋል።

ገንዘቡን ለድርጅቶቹ ያስረከቡት የሟች አለቃ ኃይለማርያም ገብረመድሀን ልጅ አይናለም ኃይለማርያምና እህታቸው ወይዘሮ ገነት ገብረ መድህን ናቸው።

ልጃቸው ወጣት አይናለም በዚህ ወቅት  እንዳለው፣አባታቸው  በህይወት እያሉ በተስካር፣ሰርግና ክርስትና እየተባለ የሚባክነውን ከመጠን ያለፈ ገንዘብ ለተቸገሩ ወገኖች መዋል አለበት በማለት ያላቸውን ይደግፉ ነበር።

የዛሬ ድጋፍም የአባቱ እምነትና ፍላጎት የነበረውን በጎ ተግባር ለማስታወስ በማሰብ መሆኑን ወጣቱ ተናግሯል።

እህታቸው በበኩላቸው " ወንድማችን ለተቸገረ መስጠት አለብን እንጂ ለተስካር  መዋል የለበትም እያለ ይመክረን  ነበር፤ እኛው የሱን ፈለግ ተከትለን ገንዘቡ  ለተቸገሩ ሰዎች ድጋፍ እንዲውል ለግሰናል" ብለዋል

 የሟች ቤተሰቦች ለልማት ማህበሩ  ያበረከቱት ገንዘብ  በዳስ ውስጥ ለሚማሩ ህጻናት ወደ ዘመናዊ ህንጻ እንዲሸጋገሩ የሚያግዝ  መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  የትግራይ ልማት ማህበር ሀብት ማሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ህሩይ ናቸው።

  የሰናይ ተግባር አዕምሮ ህሙማን እንክብካቤ ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃነ ለማ  በበኩላቸው   ቤተሰቦቹ ያደረጉላቸው የገንዘብ ድጋፍ የአዕምሮ  ህመምተኞችን ችግር ለማቃለል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

የበጎ አድራጎት ድጋፉ ለሌሎችም አርአያ በመሆን እንደሚያስተምርም ጠቁመዋል።

የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ንግስቲ ወልደሩፋኤል የሟች ቤተሰቦች ለተቸገሩ  የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳብ ያበረከቱት የገንዘብ ድጋፍ የተቀደሰ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም