ረቂቅ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ በሕብረተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና አያሳድርም ... የገቢዎች ሚኒስቴር

110
ኢዜአ፤ ታህሳስ  21/2012 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየታየ የሚገኘው የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በህዝቡ ኑሮ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያሳድር ሳይሆን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። የገቢዎች ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለንግዱ ማህበረሰብ እና ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በረቂቅ አዋጁ ላይ ዛሬ ማብራሪያ ሰጥቷል። ገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አበቤ  ረቂቅ አዋጁ የአረዳድ ችግር ተፈጥሮበት ካልሆነ በስተቀር ለአገሪቱ ያለው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። የታክሱ ዋና ዓለማም በመሰረታዊነት የሕብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻልን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ እንደሆነ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከፍተኛ የልማት ፍላጎት መኖሩን የጠቀሱት ወይዘሮ አዳነች የልማት ፍላጎት የሚሟላው አገራዊ ገቢን በተገቢው ሁኔታ መሰብሰብ ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል። በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ፖሊሲ ዳይሬክተር አቶ ሙላይ ወልዱ  በበኩላቸው  'የኤክሳይዝ ታክስ'ን ምንንት አስመልከተው ባቀረቡት ገለጻ የታክስ አሰራሩ በዓለም ላይ የተለመደና ሲተገበር የኖረ ነው ብለዋል። ኤክሳይዝ ታክስ በዋናነት በቅንጦት ዕቃዎች፣ ጤናን በሚጎዱ ምርቶችና በመሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ የሚጣል ሲሆን የገቢ ግብርን ለማሳደግ የሚውል የታክስ ዓይነት መሆኑን አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋና ምክንያት አዋጁ ሳይሻሻል ለ17 ዓመት መቆየቱና የአገሪቱ ገቢ እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነም አብራርተዋል። እንደ አቶ ሙላይ ገለጻ ነባሩ አዋጅ ለአስተዳደር አመቺ አለመሆን እና አጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሐብት አንፃር እጅግ ያነሰ ገቢ እየተሰበሰበ በመሆኑ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል። በኤክሳይዝ ታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ዕድገት ካላቸው አገራት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ዕድገት ባለባቸው የአፍሪካ አገራት ከኤክሳይዝ ታክስ የሚሰበሰበው ገቢ 2 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ዜሮ ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን አቶ ሙላይ አስረድተዋል። አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የታክስ መሰረቱን ያሰፋል የተባለ ሲሆን ዘይትና ስኳር በመሳሰሉ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ጭማሪ እንደማይደረግ ገልጸዋል። ስኳር ላይ ከዚህ በፊት ተጥሎ የነበረውን 33 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ወደ 20 በመቶ ዝቅ የተደረገ ሲሆን በዘይት ላይ ደግሞ የስብ ክምችታቸው ከ400 ግራም በላይ በሆኑት ላይ ብቻ የኤክሳይዝ ታክስ የሚጣል እንደሆነም አመልክተዋል። ረቂቅ አዋጁ ተግባራዊ ሲደረግም የልብስና የዕቃ ማጠቢያ ማሽን ላይ ይጣል የነበረው 80 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ሙሉ በሙሉ እንደሚነሳም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በተመሳሳይ  የቴሌቪዥንና ቪዲዮ ካሜራዎች ላይ ተጥሎ የነበረው 40 በመቶ ኤክሳትይዝ ታክስ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉንም ገልጸዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኤክሳይዝ ታክስ ጠቀሜታው የታወቀ ቢሆንም ጉዳዩ በአግባቡ ሊጤን እንደሚገባም ጠይቀዋል። በተለይ ደግሞ ከአልኮል ነጻ በሆኑ መጠጦች ላይ የተጣለው ኤክሳይዝ ታክስ የተጋነና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ በመሆኑ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። በአረጁ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው ታክስ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ክፍተት ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ ክፍተቱን ለመሙላት አማራጭ መንገድ መታሰብ እንዳለበትም ጠቁመዋል። የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ  ደግሞ  በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ወቅት በሕብረተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ሊያሳድሩ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት በጥንቃቄ የተዘጋጅ አዋጅ መሆኑን አብራርተዋል። ''በተለይ ረቂቅ አዋጁ መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ ቅናሽ ያስከትል ይሆናል እንጂ ለጭማሪ የሚጋብዝ ነገር አልተሰራል'' ብለዋል። በኢትዮጵያ ያለው ገበያ በሕግና በስርዓት የማይመራ ከመሆኑ አንጻር የሚያጋጥሙ ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ዶክተር እዮብ ገበያውን የማስተካከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ረቂቅ አዋጁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አይቶት ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም