ሦስት አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

49

ታህሳስ 21 / 2012 ሦስት አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቅታዊ ትኩረት ይሻል ባሉት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ። ዛሬ በተከናወነ የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ መስማማታቸውን ያረጋገጡት የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) እና ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ናቸው።

የፓርቲዎቹ ስምምነት ዋና ዓላማ፤ በአሁን ወቅት በአገሪቷ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስተዋለ የመጣውን የእርስ በእርስ ግጭትና አገሪቷ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ ለማስቀረት መሆኑም ተጠቁሟል።

በፓርቲዎቹ መካከል ያለው የፖሊሲና ስትራቴጂ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ነገር ግን አንድ በሚያደርጓቸው አገራዊ ጉዳዮች ላይ አብረው ለመስራት የጋራ ኮሚቴ ማቋቋማቸው ተመልክቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በትብብር ለመስራት በአራት ነጥቦች ላይ የተስማሙ ሲሆን፤ አንደኛው የጋራ ኮሚቴው አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የጋራ ምክክር በማድረግ መግለጫዎችን ማውጣት፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን ማካሄድ እንደሚችል ተገልጿል።

ፓርቲዎቹ የአገርን ህልውና በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀጣይ ግንኙነት በመፍጠር የሚሰሩ መሆኑም በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።

በአንድ የምርጫ ''ማንፌስቶ'' በመወዳደር ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያስችሏቸውን ውይይትና

ድርድር ከወዲሁ ለመጀመርና ከምርጫው በኋላም  የጥምር መንግስት ለማቋቋም የሚያስገድድ ሁኔታ ቢፈጠር አስፈላጊ የሆነውን ድርድርና ስምምነት ከምርጫው በፊት ለማካሄድ ተስማምተዋል።

የብሄራዊ ምክር ቤት አባልና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ማንኛው ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ልደቱ አያሌው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ የሚጋሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መስራት ይበልጥ ውጤታማነትን ያረጋግጣል።

''አገሪቷ ከፍተኛ የህልውና ፈተና ወስጥ ነች''ያሉት አቶ ልደቱ፤ ይህን የህልውና ፈተና ለመቋቋም በጋራ መስራቱ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጠውታል።

የኢትዮጵያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) ሊቀ መንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ ስምምነቱ አገሪቷ የተጋረጠባትን አደጋ ለመከላከልና የተሻለ ጠንካራ ፓርቲ ለመመስረት ነው።

ትብብሩንም ''አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት'' ወይም ''አብሮነት'' በሚል ስያሜ ለመጥራት የተስማሙ ሲሆን፤ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎትም ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መጪው አገራዊ ምርጫ አገሪቷ አሁን ባላት ቁመና ባይካሄድ ከሚሉት መካከል ሲሆኑ፤ ምርጫው ግን የግድ የሚካሄድ ከሆነ እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም