የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰራተኞች ባለፈው ክረምት የተከሏቸውን ችግኞች ተንከባከቡ

85

ኢዜአ ታህሳስ 21/2012 የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች ባለፈው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የተከሏቸውን ችግኞች በዛሬው እለት ተንከባከቡ። ባለፈው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. "በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ዛፍ" በሚል መሪ ቃል በተካሄደው አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአንድ ቀን ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉ ይታወሳል፡፡

በዚህ የችግኝ ተከላ ከተሳተፉት መካከል የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞችም በእለቱ ከ24 ሺህ በላይ ችግኞችን በኦሮሚያ ክልል ጫንጮ ወረዳ ተክለዋል።

ሠራተኞቹ በዛሬው እለትም  በስፍራው በመገኘት የተከሏቸውን ችግኞች ውሃ በማጠጣት እና በመኮትኮት የመንከባከብ ሥራ አከናውነዋል። የዛሬው እንክብካቤ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም ተገልጿል።

ችግኞቹ ወደዛፍነት እስኪቀየሩ ድረስ አስፈላጊውን ክብካቤ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ለመቀጠልም በድጋሚ ቃል ገብተዋል።

የተፋሰሶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ እንዳሉት ሚኒስቴሩ የተተከሉት ችግኞች በአግባቡ እንዲጸድቁ በግሉ ከመንከባከብ ባሻገር ከአካባቢው ነዋሪዎች ስድስት ሰዎችን በመቅጠር ችግኙን እንዲከባከቡ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የተተከሉትን ችግኞች ለሚፈለገው ዓላማ እንዲበቁ ለማድረግ የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ድጋፍ እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።

ባለፈው ክረምት በአገር አቀፍ ደረጃ 4 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው የሚታወስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም