ቀጥታ፡

በመጪው የካቲት ወር አለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችና የጨርቃ ጨርቅ ቴክኖሎጂ ኤግዚብሽን በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ኢዜአ ታህሳስ 31/2012 በመጪው የካቲት ወር አለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችና የጨርቃ ጨርቅ ቴክኖሎጂ ኤግዚብሽን በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አስታወቀ። በምክር ቤቱ የሁነቶች አስተዳደር ኃላፊ አቶ ሞገስ በቀለ እንደተናገሩት ኤግዚብሽኑ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከየካቲት 6 እስከ 8 ቀን 2012ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ ይካሄዳል። በኤግዚብሽኑ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች፣ በዘርፉ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና መሳሪያዎች እንደሚቀርቡም ተናግረዋል። አቶ ሞገስ እንደገለጹት ኤግዚብሽኑ ለአገር ውስጥ አምራቾች አዲስ የገበያ እድልና የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችልም ነው ። የአገር ውስጥ አምራቾች ከአለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የጋራ ጥምረት ለመፍጠርና ምርቶቻቸውን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ እንዲያቀርቡ እንደሚያስችልም ገልጸዋል። ኤግዚብሽኑ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በህንድ የአለም አቀፍ የማሽነሪ ኤግዚብሽን ተቋም በጋራ በመተባበር መሆኑንም ጠቅሰዋል። እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ በኤግዚብሽኑ ከ13 አገራት የተውጣጡ 220 ኩባንያዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከኤግዚብሽኑ በተጨማሪም ሴሚናሮችና 'የቢዝነስ ቱ ቢዝነስ' ውይይቶችም ይካሄዳሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም