የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ኮንፈረንስ ነገ በሰመራ ከተማ ይካሄዳል

ኢዜአ ታህሳስ 21 /2012 ከአፋርና ከአማራ ክልል ኦሮሞ ማህበረሰብ ዞን የባቲ እና ደዊሃራ ወረዳዎች የሚሳተፉበት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ኮንፈረንስ ነገ በሰመራ ከተማ ሊካሄድ ነው። ለአንድ ቀን በሚካሄደው ኮንፈረንስ  ከስድስት ወረዳዎች የተውጣጡ የሁለቱ ክልል የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

የአፋር ክልል ሰላምና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቢላይ አህመድ ለኢዜአ እንዳሉት በህዝብ ለህዝብ መድረኩ በሁለቱ ተጎራባች ክልሎች በሚገኙ 6 ወረዳዎች የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ከአፋር ክልል ተላላክ፣ ደዌ፣ አደአር እና ጭፍራ ወረዳዎች የሚሳተፉ ሲሆን ከአማራ ክልል ኦሮሞ ማህበረሰብ ዞን የሚሳተፉት ደግሞ የደዌሀራ እና ባቲ ወረዳዎች ናቸው።

"በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረኩ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖር እሴቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያግዙ ውይይቶች ይደረጋሉ" ብለዋል።

በውይይቱም ከ150 በላይ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት እንደሚሳተፉ ታውቋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዛሬው ዕለት ወደ ሰመራ ከተማ መግባት መጀመራቸውን አቶ ቢላይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም