በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ያለውን እድል ዜጎች ሊጠቀሙበት ይገባል

ታህሳስ 21 / 2012 በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ያለውን እድል ዜጎች ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ተጠቆመ። በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ላይ ያሉ የኢንቨስትመንት አቅሞችና ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክትትል ከፍተኛ የድጋፍ ባለሙያ አቶ ተሾመ ዘለቀ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በዘርፉ እምቅ ተፈጥሮዓዊ ሀብቶች እንዲሁም ለአለም አቀፍ ታላላቅ ገበያዎች ምቹ መልካ-ምድራዊ አቀማመጥና ምቹ ሁኔታዎች ይገኛሉ። ሆኖም አገሪቷ በአለም አቀፍ የውጭ ገበያ ያላት ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑን ነው የገለጹት። እ.አ.አ በ2017 ከዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግድ ገቢ የኢትዮጵያ ድርሻ 0 ነጥብ 01 ብቻ ነው ተብለዋል። ያም ሆኖ በቀጣይ ዓመታት የበለፀጉ አገሮች የወጪ ንግድ ድርሻ እየቀነሰ የታዳጊ ሀገሮች ድርሻ እንደሚጨምር የሚገመት በመሆኑ ለታዳጊ አገራት በወጭ ንግድ ገበያ ሰፊ እድሎች እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ በዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግድ ከፍተኛ ድርሻ ካላቸው አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቻይና በማምረቻ ዋጋ መናር የተነሳ ከዋጋ ተኮር የወጪ ንግድ ወደ ኢኖቬሽን  ልታተኮር ትችላለች። በመሆኑም የቻይና የዓለም አቀፍ የገበያ ድርሻ ሲቀንስ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገሮች የገበያ እድል ሊፈጥር ይችላል ብለዋል። በአገሪቷ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ተግባራዊመደረጋቸውንና በርካታ እድሎች በመኖራቸው ዜጎች እነዚህን መልካም እድሎች ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል ። በዘርፉ በአነሰተኛና መካከለኛ አቅም መሰማራት የሚቻልባቸው በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውንም አቶ ተሾመ አንስተዋል። በዘርፉም የጥጥ ልማትና መዳመጫ፣ የፈትል ፋብሪካ፣ ሰው ሰራሽ ፋይበር፣ ሽመናና ሹራብ፣ ማቅለሚያ፣ ፋሽንና ዲዛይን፣ ማሸጊያ፣ ሕትመትና ማቅለም እንዲሁም ሌሎች አማራጮችንም ጠቁመዋል። የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ንግድ፣ባሕላዊ አልባሳትና የልብስ ስፌት እና የጥልፍ ስራዎችንም አክለዋል። አቶ ተሾመ እንደገለጹት ከቀረጥ ነፃ ኤክስፖርት ማድረግ፣ የብድር አገልግሎት፣ የካፒታል ዕቃዎችንና የኮንስትራክሽን ቁሳቁስ ከቀረጥ ነፃ ማስገባት፣ የገቢ ግብር ቅነሳና ሌሎች ማሻሸያዎች በዘርፉ ተግባራዊ ከተደረጉ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ይጠቀሳሉ። አገሪቷ ለታላላቅ ገበያዎች ያላት መልክዓ-ምድራዊ ቀረቤታ፣ ሰፊ የሀገር ውስጥ ገበያ፣የበለፀጉ ሀገሮች የጉልበት ዋጋ እየጨመረ መሄድ፣  ታላላቅ ዓለም አቀፍ ገዢዎች ወደ አገሪቱ መምጣትና ሌሎች ለዘርፉ ምቹ የሆኑ እድሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፣ ለጥጥ ልማት ሊውል የሚችል 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬትና ሌሎች እድሎችንም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ የማማከር፣ የማምረት አቅም ግንባታ፣ የግብዓትና ምርት ትስስር፣ የውጪ ገበያ መረጃ አቅርቦትና ሌሎች ድጋፎችን እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል። በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አማካሪ ነስሪን መሃመድ በበኩላቸው በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ወስጥ አምራቾች በኢንደስትሪ ፓርኮች የማምረቻ ቦታ በመጠቀም ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችሉበት መንገድ የማመቻቸት ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል። የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ግብዓቶችን ከውጭ አገራት እያስገቡ ከሚያመርቱ አለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው በርካታ ኩባንያዎች ጋርም የአገር ውስጥ አምራቾች በጋራ መስራት የሚችሉባቸው እድሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት  ምክትል ዋና ጸሀፊ አቶ ውቤ መንግስቱ እንደተናገሩት የመርሃ ግብሩ አላማ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ያሉ እድሎች ላይ ግንዛቤ በመፍጠርና ዜጎች በዘርፉ እንዲሰማሩ እድል ማመቻቸት ነው። ምክር ቤቱ አገር በቀል ድርጅቶች ከውጭ አገራት ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር የሚችሉበትንና በሽርክና መስራት የሚችሉባቸውን እድሎችን ለመፍጠር ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም