የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በዘላቂነት ለመከላከል የህግ ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በዘላቂነት ለመከላከል የህግ ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ ተገለፀ
ታህሳስ 21 / 2012 በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በዘላቂነት ለመከላከል የህግ ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ ተገለፀ። ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በዘላቂነት ለመከላከል እንዲያስችል ከመገናኛ ብዙሃን የሚጠበቀው ሚና ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለምርመራ ጋዜጠኞች ተሰጥቷል። በሥልጠናው ስለ ኮንትሮባንድ ምንነት፣ ኮንትሮባንድ እና ህገ ወጥ ንግድ የሚያስከትላቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳቶችን ጨምሮ በአገሪቷ የኮንትሮባንድ ነባራዊ ሁኔታን የተመለከቱ ማብራሪያዎች በባለሙያዎች ቀርበዋል። በዚህም በአገሪቷ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ እና ፍትሃዊ የንግድ ስርአቱን እያመሰቃቀለው መሆኑን ጨምሮ የታክስ አስተዳደሩን እየፈተነው መሆኑም ተገልጿል። በጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠርና የተጠናከረ የመከላከል ስራ መስራት ጊዜ የማይሰጠዉ ጉዳይ በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው በስፋት መስራት እንደሚገባቸው ተነግሯል። የህግ ባለሙያው አቶ ሚካኤል ተሾመ፤ በአገሪቷ የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ ለመስፋፋቱ ዋነኛ ምክንያቱ የቅጣት ማነስ መሆኑን ተናግረዋል። ለአብነትም የጉምሩክ አዋጅ 859/2006 እና በ1996 ዓ.ም የወጣውና አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 352 በኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ ላይ ጥፋተኛ ሆኖ ለተገኙ ሰዎች የሚጥለው የገንዘብም ሆነ የእስር ቅጣት አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት በኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚጣልባቸው ቅጣት አነስተኛ መሆኑን የሚያውቁ በመሆኑ ችግሩ ከእለት ተዕለት መልኩንና አይነቱን ቀይሮ እየተባበሰ መምጣቱን ገልፀዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከልም የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ ላይ ያሉ የህግ ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር ተሻገር ጣሰው በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን ከእለት ተዕለት ስራቸው በዘለለ የምርመራ ስራ ላይ በማተኮር ኮንትሮባንድን እና ህገወጥ ንግድን ለማጋለጥ መስራት አለባቸው ብለዋል። አንድን ጋዜጠኛ ጋዜጠኛ የሚያስብሉት ስራዎችም በጥናት ላይ የተመሰረተ የምርመራ ስራ ሰርቶ ውጤት ማስገኘት በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚዲያ ተቋማት ለምርመራ ዘገባ ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ብለዋል። ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ከተያዙት ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች ውስጥም ግምታዊ ዋጋቸው ከገቢ ኮንትሮባንድ 3 ነጥብ 16 ቢሊዮን ብር ፤ ከወጪ ኮንትሮባንድ ደግሞ 537 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ በድምሩ ከ3 ነጥብ 697 ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ እቃዎች በመቆጣጠሪያ ጣቢያዎችና ኬላዎች መያዛቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ እቃዎቸ መካከል አዳዲስ ልብሶች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ምግብና መጠጥ፣ አደንዛዥ ዕጽ ሲጋራ፣ መድኃኒቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ መለዋወጫዎች እና የጦር መሳርያ ዋነኞቹ ናቸው። ወደ ውጪ ከሚወጡ ንብረቶች መካከል ደግሞ የውጪ አገር ገንዘቦች፣ አደንዛዥ ዕጽ፣ ጫት፣ ምግብ፣ ከብቶችና ማዕድናት ተጠቃሽ መሆናቸው ተገልጿል። የገቢ ኮንትሮባንድ በየአመቱ በአማካይ በ12 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ እያሳየ ሲሆን የወጪ ኮንትሮባንድ ደግሞ በየአመቱ በአማካይ በ28 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መሆኑን ተገልጿል፡፡