በሁለቱ ክልል ህዝብ አለመግባባትን ለመፍታተ የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሁለቱ ክልል ህዝብ አለመግባባትን ለመፍታተ የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል
ታህሳስ 21 ቀን 2012 በአፋር እና ሶማሌ ወንድማማች ህዝብ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በመፍታት እርቀሰላም ለማውረድ በሚደረገው ጥረት የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች ሚናቸውን በግንባር ቀደምነት እንዲወጡ የሰላም ሚኒስቴር አስገነዘበ።
የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባበት ለመፍታት በአዳማ ከተማ ዛሬ መምከር ጀምሯል።
በምክክር መድረኩ መክፈቻ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን እንደገለጹት በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታትና እርቀ ሰላም ለማውረድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የየክልሎቹ የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት አለባቸው።
"የአፋርና የሶማሌ ህዝብ በደም የተሳሰረ፣ ተከባብሮ የኖረና ለዘመናት አብሮነትን ሲያዳብር የኖረ ነው" ያሉት ወይዘሮ አልማዝ፣ ግጭት በማህበረሰብና በግለሰብ ደረጃ በማንኛውም ጊዜ ሊፈጠር እንደሚችል አመልክተዋል።
ይሁንና ግጭቶችን ወደ ሁከትና ደም መፋሰስ በመቀየር ለዘመነት አብሮ የኖረውን የሁለቱን ወንድማማች ህዝብ እንዲቃረን ከማድረግ እኩይ ተግባር መቆጠብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
“በደም በተሳሰሩ በሶማሌና በአፋር ክልል ህዝቦች መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት ለምን ይፈጠራል በሚል የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው" ሲሉም ወይዘሮ አልማዝ ገልጸዋል።
የመድረኩ ዓላማ የትናት የጋራ ታሪክ፣ ባህል፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መቻቻል እና አብሮነት ይበልጥ የሚዳብርበት ውሳኔ ላይ በመድረስ በሁለቱ ህዝቦች መካከል እርቀ ሰላም ማውረድና በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ማስፈን መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ወይዘሮ አልማዝ ገለጻ የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች በህዝቡ መካከል ግጭት የሚያስነሱ አካላትን በመለየት ለህግ የበላይነት መረጋገጥና ለዘላቂ ሰላም መስፈን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።
"አንዱ ሌላውን ማሰብና መተባበር ካልቻለ በግጭት አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር ሁላችንም እንጠፋለን" ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፣ የአገር ሽማግሌዎችና ዑጋዞች ሁሌም የሚወሳ በጎ ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው አስገዝበዋል።