ቀጥታ፡

መንግስት ገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት ሊያቋቁም ነው

ኢዜአ ታህሳስ 21/2012 የኢትዮጵያ መንግስት ገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት ሊያቋቁም መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የገለልተኛ ብሔራዊ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት እጩ አባላትን ለመቀበል የጥሪ ማስታወቂያም አውጥቷል። ምክር ቤቱ ገለልተኝነቱን ጠብቆ በነጻነት የሚሰራ ነው ተብሏል። አባላቱም በቁጥር 15 ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በዘርፉ የካበተ ልምድ ያላቸው፣አገርን የማገልገል መንፈሳቸው የዳበረ እንዲሆን ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈ በስራ ዘርፍ፣ በጾታና በሌሎች ገጽታዎች ብዝሃነት ያላቸው፣ የአገሪቷን ኢኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ ሁኔታ በጥልቀት የተረዱ፣ የሀሳብ ልዩነትን በመረጃና በውይይት በመፍታት የጋራ መፍትሄ የመሻት ክህሎት ያላቸው፣ ከምንም በላይ ደግሞ ለአገርና ለህዝብ ተቆርቋሪ የአገልጋይነት መንፈስ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል ተብሏል። አባላቱን የመለየቱ ሂደትም ግልጽና አሳታፊ እንዲሆን መንግስት ከዛሬ ጀምሮ የዕጩ አባላትን ጥቆማ በይፋ ለመቀበል መወሰኑንም ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ባወጣው መረጃ አስታውቋል። ገለልተኛ ብሄራዊ የኢኮኖሚ አማካሪ ምክር ቤት አባል ሆኖ ለማገልገል አቅሙና ፍላጎት ያለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ምሁራን የግል ማህደራቸውን ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት 15 ቀናት  policyunit@pmo.gov.et በሚል የኢሜል አድራሻ እንዲልኩ ተጠይቋል። መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙን በስኬት ለማስፈጸምና ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ የምሁራንና የባለሙያዎችን ምክር እንዲሁም ግብረ መልስ መቀበል ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለው። ገለልተኛ ከሆኑ ምሁራንና ባለሙያዎች ሀሳብ መቀበል የፖሊሲን አካታችነት ከመጨመር ባለፈ አገሪቷ ያለችበትን ውስብስብ የድህነትና ተያያዠ ማህበራዊ ችግሮች ለመረዳትና ዘርፈ ብዙ የፖሊሲ አማራጮችን ለመመርመርና የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማመንጨት ያስችላል። ከዚህ ባለፈ የመንግስት ፖሊሲዎች በህዝብና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ያላቸው ተቀባይነት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም