ቀጥታ፡

ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች ነው

ኢዜአ፤ ታህሳስ 21/2012 ደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር እየሰራች መሆኑ ተገለጸ።

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር  ኤድዋርድ ዞለሳ ማካያን ዛሬ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ቀኝ አገዛዝንና የአፓርታይድ ስርዓትን ለመገርሰስ በጋራ የታገሉ የረጅም ዘመናት ወዳጅ አገሮች ናቸው።

ሁለቱ አገሮች በጸረ አፓርታይድ ትግሉ በጋራ ያስመዘገቡትን የፖለቲካ ድል በኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍም መድገም እንዳለባቸው  ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትስጥም ገልጸዋል።

ሁለቱ አገሮች ቁልፍ በሆኑ የሁለትዮሽ፣ የክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ እያደረጉት ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸውም  ነው  ሚኒስትሩ ያሳሰቡት።

በርካታ ኢትዮጵያዊያን በደቡብ አፍሪካ እንደሚኖሩ ያነሱት አቶ ገዱ የዜጎችን ደህንነት በማስከበር በኩል በመቀራረብና  በትብብር መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በርካታ ደቡብ አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጋቸውንም በመግለጽ፤ የባለሀብቶቹ ቁጥር እንዲጨምር አምባሳደሩ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያርጉም  አቶ ገዱ በዚህ ወቅት አሳስበዋል።

አምባሳደር ኤድዋርድ ዞለሳ ማካያ በበኩለቸው ታዋቂው የአፍሪካ የጻነነት ታጋይ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ የአፓርታይድን ስርዓት ለመገርሰስ ስልጠና የወሰዱት በኢትዮጵያ መሆኑን በማስታወስ፤ ደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ የምንጊዜም ወዳጅ ናት ብለዋል።

በፖለቲካው ያለው የተሳካ ግንኙነት በኢኮኖሚው ዘርፍ እንዲደገም ደቡብ አፍሪካ እየሰራች ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ በአምባሳደርነት ቆይታቸውም የሁለቱን አገሮች የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል በቱሪዝም፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በጤናና መሰል ዘርፎች ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑንና በቅርቡ የትብብር ስምምነት እንደሚፈረም አምባሳደር ማካያ ገልጸዋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግስት ኢትዮጵያዊያንና የሌሎች የአፍሪካ አገር ዜጎች ደህንነትን ለማስጠበቅ እየሰራ መሆኑንም አምባሳደሩ አብረርተዋል።

ከዜጎች ደህንነት ጋር በተያያዘ መጤ ጠል ግጭቶችን ለመከላከል ያለመ ኮንፍረንስ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር በዚህ ዓመት በደቡብ አፍሪካ ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል።

ኮንፍረሱ በደቡብ አፍሪካዊያንና በሌሎች አፍሪካዊያን ዜጎች መካከል አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመከላከል የሚያስችል የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እንደሚያግዝም አምባሳደር ማኪያ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም