ቀጥታ፡

የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው

ኢዜአ፤ ታህሳስ 20/2012  በሀገሪቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፌዴራል ኀብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ። ሃገር አቀፍ የኀብረት ሥራ ማህበራት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የግብይት ትስስር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ዳሪቦ ቡሴር በዚህ ወቅት እንደገለጹት  የህብረተሰቡን የአትክልትና ፍራፍሬ ፊለጎት ለማሻሻል የገበያ ተደራሽነትን ማሳደግ ያስፈልጋል። ከፍተኛ የሀገር ውስጥ የገበያ ፍላጎት፣አምራች የሰው ኃይል፣ ምቹ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቢኖርም በዘርፉ የተደራጁ ኀብረት ስራ ማህበራት የህብረተሰቡን ፊላጎት ከማርካት አንፃር ገና ብዙ እንደሚቀራቸው ተናግረዋል። ማህበራቱ ከአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸው  ተግዳሮቶች ውስጥ ዝቅተኛ የምርት አቅርቦት መጠን፣የዋጋ መዋዠቅ፣የገበያ መዳረሻ ለማስፋት የሚያስችሉ በቂ መሰረተ ልማት አለመኖር  አቶ ዳሪቦ የጠቀሷቸው ናቸው። አላስፈላጊ የገበያ ተዋናይ ጣልቃገብነት፣ምቹ የገበያ ቦታ አለመኖርና የካፒታል እጥረት ሌላው ችግር  መሆኑንና ይህንን ለማቃለል ኤጀንሲው እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይ የአትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ ነው። አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም አምራች ኅብረት ስራ ማህበራትን  ከሸማች ኅብረት ስራ ማህበራት እና ሌሎች ገዥዎች ጋር  ቀጣይነት ያለው  ችግር ፈቺ  የግብይት ትስስር የሚፈጠርበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልጸዋል። የመድረክ  ዓላማም የአትክልትና ፍራፍሬ አምራች ኀብረት ሥራ ማህበራትን ከሸማቾች ማህበራትና ከሌሎች ተጠቃሚዎች ጋር የተሻለ የግብይት ትስስርን ለማመቻቸትና አምራቹ  ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል  መሆኑን አስረድተዋል። በኤጀንሲው የኀብረት ስራ ግብይት ባለሙያ አቶ መኳንንት አዱኛ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ዓመታዊ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መሆኑን ገልጸዋል። በኦሮሚያ፣አማራ፣ደቡብ፣ትግራይ፣ቤኒሻንጉል ክልሎች ባለፈው ዓመት ብቻ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ የሀገር ውስጥ ግብይት መፈጸሙን አስታውሰዋል። ከገበያ መዳረሻዎችም መካከል   ሸማች ኅብረት ሥራ ማህበራት፣ ኢትፍሩት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች አዲስ አበባ አትክልት ተራና ማረሚያ ቤቶች ይገኙበታል። በውጭ ገበያም አውሮፓ፣ ጅቡቲ፣ ሱማሌ ላንድ፣ መካከለኛው ምሰራቅ እስያ መድረስ መቻሉን የገለጹት ባለሙያው  በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት 120 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ አመልክተዋል። ባለፈው ዓመት የምርት አቅርቦት እጥረት በማጋጠሙ 365 ኩንታል የማንጎ ምርት ብቻ ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረባቸው የተናገሩት ደግሞ የአሶሳ አትክልትና ፍራፍሬ የግብይት ህብረት ስራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልደዳዊት ተካ ናቸው። ዘንድሮ ከ16 መሰረታዊ ማህበራት 8 ሺህ ኩንታል በመሰብሰብ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውንና ከዚህም ከሽያጩም  ትርፍ እንደሚጠቅ  ተናግረዋል። የሀረማያ አካባቢ የገበሬዎች ኀብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ አብደላ በበኩላቸው እስካሁን ባለው የስራ እንቅስቃሴ በምስራቅ ሐረርጌ  ከ11 ሺህ ለሚበልጡ የአትክልት አምራቾች የገበያ ትስሰር መፍጠራቸውን ገልጸዋል። በተያዘው ዓመት እስከ 50 ሺህ ኩንታል የተለያዩ አትክልቶች ከአርሶ አደሮች ላይ በተመጣጣኝ ዋጋ በመረከብ ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውንም አስረድተዋል።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም