ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ተጀምሯል

ኢዜአ ታህሰሳስ 20/2012 የኢትዮጵያ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ዛሬ ተጀምሯል። በውድድሩ የመክፈቻ ቀንም ስድስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል። በሻምፒዮናው በሁለቱም ጾታዎች ከአማራ ክልል ውጪ ስምንቱ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ይሳተፋሉ። በተጨማሪም ከአማራ ክልል የደብረብርሃንና የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላትም የሚሳተፉ ሲሆን ወንድ 176 ሴት 148 በድምሩ 324 አትሌቶች በሻምፒዮናው ተሳታፊ ናቸው። ሻምፒዮናው ከ18 ዓመት በታችና ከ16 ዓመት በታች በሚል በሁለት የእድሜ ዘርፎች የሚካሄድ ነው። ከ18 ዓመት በታች ላይ እድሜያቸው 16 እና 17 የሆኑ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ከ16 ዓመት በታች ላይ እድሜያቸው 15 የሆኑ አትሌቶች ይሳተፋሉ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ተሳትፎ ንዑስ የስራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ ለኢዜአ እንደገለጹት ሻምፒዮናው ለፕሮጀክት አትሌቶች የውድድር እድል መፍጠር አላማ ያደረገ ነው። ለአትሌቲክሱ እድገት መሰረት የታዳጊና ወጣቶች አትሌቲክስ ፕሮጀክቶች መሆናቸውንና በዚህ ረገድም በፕሮጀክቶች ለሚሳተፉ አትሌቶች የውድድር አማራጮችን ማስፋት ያለው ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል። በሻምፒዮናው ላይ የተሻለ ብቃት የሚያሳዩ አትሌቶች ወደ አትሌቲክስ ክለቦች የመግባት እድል እንደሚመቻችላቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች በየዓመቱ በሚካሄደው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ እንደሚሳተፉም አመልክተዋል። በሻምፒዮናው ላይ በሚያስመዘግቡት ውጤትም በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመሳተፍ እድል እንደሚያገኙ ነው አቶ አስፋው ያስረዱት። አትሌቶችና የአትሌቶች አሰልጣኞች እርስ በእርስ የልምድና የተሞክሮ ልውውጥ እንዲያደርጉም ሻምፒዮናው ምቹ መደላድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ከተካሄዱ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አብዛኞቹ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ከነበሩት ሻምፒዮናዎች በተቀመጠው የእድሜ ገደብ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አትሌቶችን ይዘው እንደመጡ ጠቅሰዋል። ፌዴሬሽኑ ባለው የአትሌቶች የመረጃ ቋትና ሌሎች ማስረጃዎች መሰረት የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ ላይ ማጣራት እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በማጣራት ሂደት ውስጥ ከእድሜ በላይ የተወዳደሩ አትሌቶች ከተገኙ ከሻምፒዮናው የማሰናበትና ሜዳሊያ የመንጠቅ አርምጃ እንደሚወሰድም ነው አቶ አስፋው ያብራሩት። የአማራ ክልል በሻምፒዮናው ላይ ያልተሳተፈበት ምክንያት ለፌዴሬሽኑ እንዳላሳወቀ አክለዋል። የኢትዮጵያ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ሲጀመር ስድስት የፍጻሜ ውድድሮች ተካሄደዋል። ከ18 ዓመት በታች አሎሎ ውርወራ ወንድ በለስቲ ሽቴ ከደብረብርሃን የአትሌቲከስ ማሰልጠኛ ማዕከል የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን ጆን ኡመድ ከጋምቤላ ክልል የብር፣ እሱባለው አስራት ከደቡብ ክልል የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። ከ18 ዓመት በታች ሴት የዲስከስ ውርወራ ዝናሽ ማቲዎስ ከኦሮሚያ ክልል፣ አማረች አለምነህና የኔሰው ያረጋል ከደብረ ብርሃን የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የብርና ነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ አትሌቶች ናቸው። ከ16 ዓመት በታች ሴት 400 ሜትር ፅጌሬዳ ዓለምሸት ከትግራይ ክልል፣ ማሚ መኩሪያና ራሔል ማቲኬ ከኦሮሚያ ክልል ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ከ16 ዓመት በታች ወንድ 400 ሜትር ተመስገን ቸኮለ ከትግራይ ክልል አሸናፊ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪዎቹ ቀነኒሳ ተሾመ እና ጎሳ ለገሰ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል። ከ16 ዓመት በታች ሴት 800 ሜትር አትሌት ሴዶ በሻና አትሌት አስቴር አራሪ ከኦሮሚያ ክልል ተከታትለው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ይዘው የገቡ ሲሆን ፀጉ ታፈረ ከትግራይ ክልል ሶስተኛ ወጥታለች። ከ16 ዓመት በታች ወንድ 800 ሜትር ሲሳይ ካሱ ከኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሲሆን አብርሃ ታደሰና አረዶም ፋንታዬ ሁለ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በዛሬው ውድድር የኦሮሚያ ክልል ሶስት የትግራይ ሁለት የደብረብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አንድ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝተዋል። ሻምፒዮናው ነገም ሲቀጥል 10 የፍጻሜ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል። የኢትዮጵያ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ታህሳስ 25 2012 ዓ.ም ይቆያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም