ቀጥታ፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ርዕስቱ ይርዳው በየም ልዩ ወረዳ የልማት ስራዎችን ጎበኙ

ኢዜአ ታህሳስ 20/2012.. የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ርዕስቱ ይርዳው በየም ልዩ ወረዳ በመገንባት ላይ የሚገኙ የተለያዩ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ተዘዋውረው ጎበኙ። በምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ከተጎበኙት የመሠረተ ልማቶች ግንባታዎች መካከል የሳጃ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ በሳጃ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅ፣ የግብርና ልማት ስራዎችና የፎፋ ከተማ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት ግንባታ ስራዎችን ይገኙበታል። በጉብኝቱ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል። የሳጃ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር በልስቲ ታፈረ ለጎብኚዎቹ እንደገለጹት፤ የሳጃ የመጀመሪያ ሆስፒታል በልዩ ወረዳውና ለሌሎች አጎራባች ወረዳዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ሆስፒታሉ ለተገልጋዩ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የሰው ኃይል፣ የላቦራቶሪ ቁሳቁስ፣ የጥገና እና የማስፋፊያ ግንባታ እንዲካሄድለት የክልሉን ድጋፍ ጠይቀዋል። የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አቅናው ሀውዛ ሆስፒታሉ የተገልጋዩን እርካታ እንዲያረጋግጥ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን በዚሁ ጊዜ ቃል ገብተዋል። በቅርብ ጊዜም ለሆስፒታሉ "በተለይ የጠቅላላ ሐኪሞችን ቁጥር ለማሳደግ እና የላቦራቶሪ ጥገና ይደረጋል" ብለዋል። ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ አቶ ርዕስቱ ይርዳ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት አድንቀው፤ የሆስፒታሉን ግቢ ለዓይን ማራኪና ለታካሚዎች ምቹ ለማድረግ የአረንጓዴ ልማት ስራ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል። የሆስፒታሉ የግንባታ ማስፋፊያ ጥያቄን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፤ በክልሉ ዘንድሮ አዲስ ግንባታ የመጀመር ዕቅድ አለመኖሩን ገልጸው ጥያቄው ወደ ፊት በአገር አቀፍ ደረጃ የሆስፒታሎች ማስፋፊያ መርሃ ግብር ጋር አብሮ የሚመለስ መሆኑን አመላክተዋል። አቶ ርዕስቱ በሳጃ ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪ ኮሌጅ ባደረጉት ጉብኝት ኮሌጁ በካይዘን አመራር የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል። በኮሌጁ የሚገኙ የተለያዩ የትምህርት መስኮች ስራ መፍጠር የሚችሉ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጠንክሮ እንዲሰራ መልዕክት አስተላልፈዋል። በልዩ ወረዳው የሚታወቀው የዶሪ ቀበሌ የግብርና ልማት ስራን ባደረጉት ጉብኝት የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ለአስተዳደሩ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። በፎፋ እየተካሄደ ያለው የውስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ ግንባታ በጥራትና በፍጥነት ተከናውኖ በጊዜ እንዲጠናቀቅ ክትትል እንዲደረግ መመሪያ አስተላልፈዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በየም ልዩ ወረዳ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ በሳጃ ከተማ እየተወያዩ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም