የምርጫ ቦርድ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን ለማሳደግ ድጋፍ እየተደረገለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምርጫ ቦርድ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን ለማሳደግ ድጋፍ እየተደረገለት ነው
ኢዜአ ታህሳስ 20/2012.. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) አስታወቀ። 'በፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና በምርጫ ህግ ማዕቀፎች' ላይ ለሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የተዘጋጀውና ትናንት የተጀመረው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬም ቀጥሏል። በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው መድረክ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲ.ፒ) ትብብር የተዘጋጀ ነው። በመድረኩ ከ106 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ ሴት አመራሮችና አባላት እየተሳተፉ ይገኛል። ዩ.ኤን.ዲ.ፒ በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቋማትን አቅም መገንባት፣ መልካም አስተዳደርን ማጠናከርና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን ማሳደግ ዓላማ ያደረገ "የአስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ መርሃ ግብር" እንደ አውሮጳወያን አቆጣጠር በ2017 ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። መርሃ ግብሩ ለአራት ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን 40 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦለት ነበር። ዴሞክራሲያዊ አሳታፊነት ማሳደግና ዘላቂ ሰላም ማምጣት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለበት የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም የዜጎች ተሳትፎን ማሳደግ የመርሃ ግብሩ ምሶሶዎች ናቸው። መርሃ ግብሩ በዴሞክራሲ ግንባታ ላይ በሚሰሩ 11 ተቋማት ላይ የሚተገበር መሆኑም ተመልክታል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ፣ የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መርሃ ግብሩ ተግባራዊ የሚደረግባቸው ተቋማት ናቸው። ኢዜአ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቋማዊ የማስፈጸም አቅሙን ከማጠናከር አኳያ በመርሃ ግብሩ እየተደረገለት ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ ዩ.ኤን.ዲ.ፒን ጠይቋል። በዩ.ኤን.ዲ.ፒ የአስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ መርሃ ግብር የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተባባሪ አቶ ደቻሳ መርጋ እንዳሉት፤ በመርሃ ግብሩ ለቦርዱ የቴክኒክ ድጋፎች እያደረገ ነው። ለቦርዱ ሰራተኞች ስልጠዎችን በመስጠት የማስፈጸም አቅማቸው እንዲጎለብት የማድረግና ተቋማዊ አቅሙን የማጎልበት ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። እስከ አሁን ድረስ ለቦርዱ የቁሳቁስና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በዚህም ለውጥ እየመጣ መሆኑን አክለዋል። ከመርሃ ግብሩ ዓላማዎች መካከል ተቋማዊ ለውጥን መደገፍ አንዱ ሲሆን ''ቦርዱ የሚያቀርባቸውን የድጋፍ መስኮች በመገምገም አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል'' ብለዋል። እንደ አቶ ደቻሳ ገለጻ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚያወጣውን ዓመታዊ የስራ ዕቅድ መሰረት በማድረግና ለምርጫ ቦርድ የሚያስፈልጉ ደንቦችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ድጋፍ እየተደረገ ነው። ቦርዱ ሴቶች በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ስራ እያከናወነ መሆኑን አክለዋል። በመርሃ ግብሩ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተደረጉ ድጋፎች ላይ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያካሂድና በጥናቱ የሚገኙ ግኝቶችን መሰረት በማድረግ ድጋፉ እንደሚቀጥል አቶ ደቻሳ ጠቁመዋል። የአስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ መርሃ ግብር በቀጣይ ሁለት ዓመታት አገራዊ ለውጡን መሰረት በማድረግ ለምርጫ ቦርድ የሚያደርገው ድጋፍ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። መርሃ ግብሩ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2021 ይጠናቀቃል። 'በፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና በምርጫ ህግ ማዕቀፎች' ላይ ለሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ ይጠናቀቃል።