ቀጥታ፡

የሀገሪቱን ስፖርት ፖሊሲ ማሻሻል እንደሚያስፈለግ ተገለጸ

ኢዜአ ታህሳስ 20/2012 የሀገሪቱን ስፖርት እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ አሁን ያለውን የዘርፉ ፖሊሲ ማሻሻል እንደሚያስፈለግ ተገለጸ። በስፖርት ሪፎርም ፕሮግራም ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ አሁን በስራ ላይ ያለውን የስፖርት ፖሊሲ ችግሮችና ቀጣይ ምን ቢሆን ይሻላል በሚል የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ ሳሙኤል ስለሽ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የስፖርት ፖሊሲ የግል ሴክተሩን የማያበረታታና ስራውን ለመንግስት ብቻ የሰጠ ነው። ይህም ስፖርቱ የራሱን ገቢ እንዳያመነጪ፣ የመንግስት ጠባቂና በዘርፉ የተሳትፎ ጉዳይ እንጂ የልማት አንዱ አካል እንዳይሆን አድርጎታል። በርካታ የግል ባለሃብቶች በስፖርቱ ዘርፍ ለመሰማራት ቢያቅዱም ፖሊሲው አስሮ ስለያዛቸው በዘርፉ መሳተፍ አልቻሉም። የሀገሪቱ የስፖርት ፖሊሲ ላለፉት 22 ዓመታት በስራ ላይ እንደቆየ ያመለከቱት አቶ ሳሙኤል ይህም ሌላው አለም የደረሰበትን ደረጃ ከግምት አስገብቶ ሊሻሻልና የግል ሴክተሩ ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። እንደ ጽሁፍ አቅራቢው ገለጻ ይህ ካልሆነ በመንግስት በጀት ስፖርቱን የማሳደግ፣እንደ ሀገር የሚያበረከተውን የልማት አስተዋጽኦና የህዝቦችን ማህበራዊ ትስስር የማዳበር ድርሻው እንደቀጨጨ ይቀጥላል። እንደ ሀገር የስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት፣ በአስልጣኝነትም ሆነ በዳኝነት ብቁና በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገው ጥረት አስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። የስፖርት ፖሊሲው አሁን ላይ በዘርፉ የሚሰተዋሉ ግድፈቶችን ሁሉ በሚያስተካከል መልኩ ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ባዝዛው ጫኔ በበኩላቸው "በስራ ላይ ያለው ፖሊሲ በርካታ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ያደረገ ቢሆንም አሁን ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ሊሻሻል ይገባል “ብለዋል። ስፖርት የዜጎች መሰረታዊ መብት ተደርጎ እንደ ሀገር እንዲሰራበት ያስቻለ ፖሊሲ ቢሆንም ተሳትፎነትን ከማሳደግ ባለፈ የገቢ ምንጪ እንዲሆንና የሀገርን ገጽታ በሚያጎላ መልኩ እንዲሰራበት በማድረግ ረገድ ውስንነት ያለበት ነው። የፖሊሲውን ጠንካራ ጎኖች በማስቀጠል  በስፖርቱ ዘርፍ የሚሰማሩ  ሁሉ እንዲሳተፍ በሚያደርግ መልኩ መሻሻል ያስፈልጋል። የአማራ ክልላዊ መንግስት ፖሊሲው እንዲሻሻል በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ የራሱን ድርሻ ለመወጣት በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል። በስራ ላይ ያለው ፖሊሲ መሻሻል እንዳለበት ወስነው በዘርፉ ልምድ ባላቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በማስጠናት መካተትና መቀነስ ያለባቸውን ሃሳቦች እያስገመገመ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢፌዴሪ ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ ናቸው። “ስፖርት አንድን ሀገር በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ዘርፉ ለማሳደግ ከፍተኛ ድርሻ ቢኖረውም ዘርፎ የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ አይደለም “ ብለዋል። የፖሊሲው መሻሻል ፈጥኖ ተግባራዊ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ተጨማሪ ግብአቶች በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡም መዕልክታቸወን አስተላልፈዋል። በንቅናቄ መድረኩ የአማራ ክልል የስፖረት ዘርፍ አመራሮች፣ባለሙያዎችና የኢፊዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም