ቀጥታ፡

ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ለወጣቱ የተሻለ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባ የድሬዳዋ ወጣቶች ተናገሩ

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ታህሳስ 20 / 2012 መንግስት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍና ማበረታቻ በማጠናከር የወጣቱን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ማስፋት እንዳለበት የድሬዳዋ ወጣቶች ተናገሩ። አስተያየታቸው ለኢዜአ የተናገሩት ወጣቶች በቻይናው ዎሺ ነምበር ዋን የጥጥ  ክር ማምረቻ ውስጥ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው የድሬዳዋ ወጣቶች ናቸው። የቻይናው ዎሺ ነምበር ዋን ዓለም አቀፍ የሱፍ ክር ማምረቻ በ220 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደረጃውን የጠበቀ የሱፍ ክሮች ማምረቻ የፋብሪካ ሼድ በድሬዳዋ እየገነባ ይገኛል፡፡ ዎሺ ነምበር ዋን አምና የጀመረው የፋብሪካ ሼዱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ አጠናቆ በአሁኑ ወቅት የጥጥ ክር ማምረት ጀምሯል፡፡ ለ400 የአካባቢው የተማሩና ያልተማሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩም ታውቋል፡፡ በፋብሪካው የሥራ ዕድል ያገኘችውና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተመረቀችው ወጣት ትርሲት ዳቢ የኢንቨስትመንት መስፋፋት ለወጣቱ ህይወትና ኑሮ መለወጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ለኢዜአ ተናግራለች፡፡ መንግስት በተለይ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚያደርገው ድጋፍና ማበረታቻ በማጠናከር የወጣቱን ተስፋ ማለምለም እንዳለበት አሳስባለች፡፡ ከድሬዳዋ ኢትዮ-ጣሊያን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የተመረቀችው ወጣት ሳምራዊት ዮሐንስ የእዚህ ፋብሪካ መገንባት እሷንና መሰል ወጣቶችን እቤት ውስጥ ከመዋል እንደታደጋቸው ተናግራለች፡፡ "የድሬዳዋ አስተዳደር ለባለሃብቱ የሚያደርገው ድጋፍ ሥራ አጥቶ በየስፍራው ለሚውለው ወጣት መፍትሄ ያመጣል፤ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግ ይገባል" ብላለች። የእርሻ መሬታቸውን ለኢንቨስትመንት ልማት ከለቀቁና በማምረቻው የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው የአሰሊሶ ገጠር ቀበሌ ወጣቶችና እናቶች መካከል ወይዘሮ ሚሰራ ዩያ በበኩላቸው "ፋብሪካው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መተሳሰሩ ጥሩ እርምጃ ነው" ብለዋል፡፡ "ለተማሩትም ሆነ ለኛ የሚከፈለው የደመወዝ መጠን አነስተኛ ነው፤ በእዚህ ደመወዝ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ይከብዳል" ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ የግንባታ ተቆጣጣሪ ሠራተኛ ወጣት ብሩክ አስረስ ከሚያገኘው ደመወዝ የበለጠ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ቀጣዩን የሕይወት ጉዞውን የሰመረ እንደሚያደርገው ተናግሯል፡፡ "ይህ ሁሉ የሥራ ዕድል የተፈጠረው የቻይና ባለሃብቶች ድሬዳዋ በመምጣታቸው ነው፤ መንግስት የሌሎች ሀገሮች ምድሬዳዋ እንዲገቡ በማበረታታትና በመደገፍ ለድሬዳዋ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አለበት" ብሏል፡፡ የዎሺ ነምበር ዋን የክር ማምረቻ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጃንግ ሻን ሜንግ ከሁለት ዓመት በፊት ከፌደራልና ከድሬዳዋ አስተዳደር በተደረገላቸው ድጋፍ በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሚገኝ 51 ሄክታር መሬት ላይ ከሁለት ዓመት በፊት የፋብሪካውን ሼድ የግንባታ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ሥራ  በመጠናቀቁ በአሁኑ ወቅት የሱፍ ክር ማምረት መጀመሩንና ለ400 ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል። ከወር በኋላ የሠራተኞች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ እንደሚደርስ ጠቁመው፣ ከሁለት ዓመት በኋላ የፋብሪካው ግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለ3 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል። ለፋብሪካው ግንባታ በአጠቃላይ 220 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መመደቡን የገለጹት ሚስተር ጃንግ፣ ፋብሪካው የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በአገሪቱ ምጣኔ ሃብትና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ማምረት የጀመራቸውን ክሮች ወደቻይና፣ አውሮፓና አሜሪካ እየላከ መሆኑን ጠቁመው "በቀጣይም ከእንስሳት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የክር ምርቶችን ያመርታል" ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን እንደተናገሩት፣ መንግስት ባለፉት 5 ዓመታት ካስገነባችው 11 ፓርኮች አንዱ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሆኑንና ፓርኩ ተጠናቆ ባለሃብቶችና አልሚዎችን እየጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል። ለፓርኩ ከተዘጋጀው 4 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመጀመሪያ ምዕራፍ በ150 ሄክታር መሬት ላይ 15 የፋብሪካ  ሼዶች፣ የመኖሪያና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ተገንብተው ለባለሃብቱ መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡ "በፓርኩ ውስጥ ሥራ ለመጀመር የበርካታ አገሮች ባለሃብቶች ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ጋር እየተነጋገሩ ናቸው፤ ከእነዚህ ውስጥም አራት የጣሊያን፣ የቻይናና የሌሎች አገሮች ባለሃብቶች ሥራ ለመጀመር እየተዘጋጁ ነው" ብለዋል፡፡ የዎሺ ነምበር ዋን የቻይና ክር ማምረቻም የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታውን በ80 ሚሊዮን ዶላር አጠናቆ ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ "እነዚህ ተግባራት ለወጣቶች ትርጉም ያለው የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፤ ከአገራችን ወደውጭ የሚላኩ ምርቶችን ዓይነትና መጠን ይጨምራል፤ የቴክኖሎጂ ሽግግሩንም ያፈጥናል" ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ስኬታማ እንዲሆን ከድሬዳዋ አስተዳደር ጋር በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም