የጉራጌ ህዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ እያገኘ አይደለም - አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የጉራጌ ህዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ እያገኘ አይደለም - አስተያየት ሰጪዎች
ኢዜአ ታህሳስ 19/2012 "የጉራጌ ህዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ እያገኘ አይደለም" ሲሉ በጉራጌ ዞን እጃ ወረዳ በተካሄደ ስብሰባ ላይ የተገኙ አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ። የጉራጌ ህዝብ የልማት ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ምላሽ የሚያገኘው የተጀመረው ለውጥ ሰኬታማ እንዲሆን ተጋግዞ መስራት ሲቻል መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ርዕስቱ ይርዳው ምላሽ ሰጥተዋል። የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ርዕስቱ ይርዳው ዛሬ በጉራጌ ዞን እጃ ወረዳ ተገኝተው በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ የህዝብ ተወካዮች በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ተወያይተዋል። የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የአካባቢው ህዝብ ተወካዮች እንደገለጹት፤ ህዝቡ የሚያነሳቸው የመልካም አስተዳደር፣ መዋቅር፣ የልማትና የጸጥታ ጥያቄዎች በተገቢ መጠን ምላሽ እያገኙ አይደለም። የህዝብ ችግር ለመፍታት በህብረተሰቡ አማካኝነት የተመሠረቱ ነባር የማህበራዊ አገልግሎት አደረጃጀቶች ውጤታማ ያለመሆናቸውን ገልጸዋል። “ችግሮቻችንን በራሳችን አቅም እንድንፈታና የሚመጥነንን ልማት እንድናገኝ እየተደረገ አይደለም” ብለዋል። በዞኑ ያሉ የመሠረተ-ልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ እንዲሁም የህብረተሰቡ ባህልና ቋንቋ ለማዳበር የሚያስችል አማራጭ እየጠበበ መምጣቱንም ገልጸዋል። ህብረተሰቡ የሚመጥነውን ልማት እንዲያገኝ የክልሉ መንግስት የማስተባበርና የመምራት ሚናውን እንዲወጣም ጠይቀዋል። ከተሳታፊዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ - መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የጉራጌ ህዝብ የልማት ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ምላሽ የሚያገኘው የተጀመረው ለውጥ ለውጤት እንዲበቃ መተጋገዝ ሲቻል ነው። "ጥቅሜን ያስከብራል" ብሎ ህዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች ውጤት ሊያመጡ በሚችሉበት መንገድ እንዲፈፀሙ እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል። “የምንሠራው ስራ በጥንቃቄ፣ በጥበብና ህዝቡን ሊጠቅም በሚችል መልኩ መጓዝ አለበት” ያሉት አቶ ርዕስቱ፤ ህዝቡ አመራሩን እንዲያግዝ ጠይቀዋል። ዞኑን ያጋጠመው የሰላምና ጸጥታ መደፍረስ ችግር እንዲፈታ አመራሩ በትኩረት እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል። የደኢህዴን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በሰጡት ምላሽ “ጉራጌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማጣፈጫ ነው” ብለው ህብረተሰቡ ሰላሙን አስጠብቆ ልማቱን ማስቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ከአደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽ በክልሉ በርካታ ዞኖች ክልል እንሁን በሚል ያነሱት ጥያቄ በምክክር ምላሽ የሚያገኝበት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በዞኑ ግጭት ውስጥ የገቡ የህብረተሰብ ክፍሎች የእርስ በርስ ፉክክር ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ውስብስብ እንዳደረገውም ተናግረዋል። ይህን ችግር በመፍታት የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ዕለት ተዕለት እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸው፤ አመራር አባላቱ በቅንነት በመስራት ለችግሩ ዕልባት እንዲመሰጡ ጠይቀዋል። የዞኑ አስተዳደር አቶ መሐመድ ጀማልም፤ በዞኑ የመሠረተ ልማት ስራዎች ችግር ውስጥ ያሉ መሆናቸውን አምነው፤ መፍትሔ ለማምጣት የጉራጌ ተወላጆች በጋራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል። በዞኑ ሠላምን በማረጋገጥ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። የአደረጃጀት ጥያቄ በህገ-መንግስቱ መሠረት መጠየቁ ተገቢ መሆኑን ገልጸው፤ ጥያቄው የፖለቲካ ንግድ የሚካሄድበት እንዳይሆን ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው አስገንዝበዋል።