ቀጥታ፡

በፕሪሚየር ሊጉ በተደረገ ጨዋታ ሰበታ ከተማና ፋሲል ከተማ ሶስት አቻ ተለያይተዋል

ኢዜአ ታህሳስ 19/2012 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ሰበታ ከተማና ፋሲል ከተማ ሶስት አቻ ተለያዩ። በስታዲየም ግንባታ ምክንያት ጨዋታዎቹን በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረገ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ዛሬ ፋሲል ከነማን አስተናግዶ ሶስት አቻ ተለያይቷል። ለሰበታ ከተማ ግቦቹን ፍጹም ገብረማርያም ሁለት አስቻለው ግርማ አንድ ያስቆጠሩ ሲሆን አንዱ የፍጹም ገብረ ማርያም ግብና የአስቻለው ግርማ ጎል መደበኛው 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪ ሰአት ላይ የተገኙ ናቸው። ፋሲል ከነማ በጋናዊው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ኦሴይ ማውሊ፣ሽመክት ጉግሳና ሙጂብ ቃሲም ግቦች 3 ለ 1 ይመራ የነበረ ቢሆንም በጭማሪ ሰአት የተቆጠሩበት ግቦች ሶስት ነጥብ አሳጥተውታል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ስዩም ከበደና የሰበታ ከተማው አሰልጣኝ የቀድሞ ክለቦቻቸውን የገጠሙበት ጨዋታም ነው። ስዩም ከበደ ከነሐሴ 2010 ዓ.ም እስከ መጋቢት 2011 ዓ.ም ለስምንት ወር ሰበታ ከተማን ያሰለጠኑ ሲሆን ውበቱ አባተ ባለፈው የውድድር ዓመት የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ እንደነበር ይታወሳል። ውጤቱንም ተከትሎ ፋሲል በስምንት ነጥብ በነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ሲረጋ ሰበታ ከተማ ነጥቡን ወደ አምስት ከፍ በማድረግ ከነበረበት 14ኛ ደረጃ ወደ 13ኛ ደረጃ መምጣት ችሏል። የፕሪሚየር ሊጉ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የመጨረሻ መርሃ ግብር ነገ የሚካሄድ ሲሆን የእምናው የሊጉ አሸናፊ መቐለ ሰብዓ እንደርታ የሊጉን መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በትግራይ ስታዲየም ያስተናግዳል። ትናንት በሊጉ የአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ስድስት ጨዋታዎች ተካሄደዋል። ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና አንድ አቻ ሲወጡ፤ ሀዲያ ሆሳዕና ከባህርዳር ከተማ ሁለት እኩል ሲጠናቀቅ ስሁል ሽረ ከአዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል። ወደ ጅማ ያቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ በጅማ አባ ጅፋር 2 ለ 1  ተሸንፏል። ሀዋሳ ከተማ በሜዳው በሲዳማ ቡና 3 ለ 1 ሲሸነፍ በተመሳሳይ ወላይታ ድቻም በሜዳው ከወልቂጤ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ 1 ለ 0  ተሸንፏል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ10 ነጥብ ሲመራ፤ ሲዳማ ቡና በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ ፋሲል ከነማና ባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ ስምንት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል። ስሑል ሽረ በአምስት ነጥብ፣ድሬዳዋ ከተማ በአራት ነጥብና  ሀድያ ሆሳዕና በሁለት ነጥብ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለ ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በአምስት ግቦች ሲመራ፤ ማሊያዊው የባህርዳር ከተማ አጥቂ ማማዱ ሲዲቤና የኢትዮጵያ ቡናው እንዳለ ደባልቄ በተመሳሳይ አራት ጎሎች ይከተላሉ።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም