ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ራሳቸውን ብቁ የማድረግ ስራ መስራት ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ራሳቸውን ብቁ የማድረግ ስራ መስራት ይገባቸዋል
ኢኤአ ታህሳስ 19 / 2012 ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ራሳቸውን ብቁ የማድረግ ስራ መስራት እንደሚገባቸው ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ። በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት የመቀየር ስራም ከቤተሰብ መጀመር እንዳለበት ነው አመራሮቹ የተናገሩት። በፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና የምርጫ ህግ ማዕቀፎች ላይ ለሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው በዚህ የሁለት ቀናት መድረክ ላይ ከ106 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ አመራሮችና አባላት እየተሳተፉ ነው። ኢዜአ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ የሚኖራቸውን ተሳትፎ በምን አይነት መልኩ ማሳደግ አለባቸው በሚለው ዙሪያ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግሯል። የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኢዴፓ) ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጽጌ ጥበቡ በፓርቲያቸው በአባልነትና በከፍተኛ አመራርነት ለ18 ዓመት ማገልገላቸውን ይገልጻሉ። በፓርቲው ውስጥ ባሳለፉት ቆይታም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋና ቀላል እንዳልነበሩ ይናገራሉ። ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች ለመቋቋም "የሌሎችን መልካም እድል መጠበቅ ሳይሆን ራሳቸውን ለማብቃት ትግል ማድረግ" እንዳለባቸውም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከፍተኛ አመራሮች ወንዶች በመሆናቸው ሴቶች ወደ ፖለቲካ ተሳትፎው ለመምጣት ፈተና እንደሆነባቸውም አመልክተዋል። ይሄንንም ችግር ለመፍታት ሴትን ያላሰተፈ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ የትም እንደማያደርስ ጠንቅቀው የሚያውቁ ወንድ የፖለቲካ አመራሮች ሊኖሩ እንደሚገባና ፓርቲዎችም በዚህ ላይ መስራት እንዳባቸውም ይገልጻሉ። የኦሮሚያ ነጻነት ብሔራዊ ፓርቲ የሴቶች ጉዳይ ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ነስሪን ሱሌይማን በበኩላቸው ሴቶች በማህበረሰብ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዳያድግ ተጽእኖ የሚጀምረው ከቤተሰብ እንደሆነ ይገልጻሉ። ቤተሰብ "ሴት ተምራ የትም አትደርስም፤ ምንም አታመጣም" የሚሉ አመለካከቶች ሴቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ሚናቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል። ይሄን ሰብሮ ወጥቶ በፖለቲካ ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ሴቶች የራስ መተማመናቸውንና ራሳቸውን የመግለጽ አቅማቸውን ማዳበር እንደሚገባቸውና ያለውን ችግር የመፍታት ስራም ከቤት እንደሚጀመር አመልክተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አጀንዳዎችን በፖለቲካ ፕሮግራሞቻቸው ውስጥም በማካተት ትኩረት ሰጥተው መስራት አለባቸው ብለዋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉዴፓ) አባል ወይዘሮ አለምነሽ ይባስም ሴቶች ከአጠቃላይ ህብረተሰቡ ከግማሽ በላይ ያለውን ድርሻ እንደሚይዙ ቢታወቅም ይሄ በከፍተኛ የፖለቲካ አመራርነት ቦታዎች ላይ እንደማይንጸባረቅ ገልጸዋል። ሴቶች አቅም እያላቸው የፖለቲካ ተሳትፏቸው የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነና ይሄም እንዲሻሻል ሴቶችን ተሳትፎቸውን የሚያሳድጉበትን ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት ተናግረዋል። ሴቶች በፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ሚዛናዊ የሆነ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል አመራሮቹ። በፖለቲካ ብቻም ሳይሆን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨባጭ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸውም አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የሴቶች ተሳትፎ በፓርላማ 38 በመቶ፣ በካቢኔ ደግሞ 50 በመቶ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ያም ቢሆን ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎችና በአጠቃላይ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ አናሳ እንደሆነ የዘርፉ ተዋናዮች ይገልጻሉ።