አዲሱ አዋጅ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዮችን ያከተተ ነው --- ምርጫ ቦርድ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ አዋጅ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዮችን ያከተተ ነው --- ምርጫ ቦርድ
ኢኤአ ታህሳስ 19 / 2012 አዲሱ የኢትዮጵያ የምርጫ ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑ ተገለጸ። በፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና የምርጫ ህግ ማዕቀፎች ላይ ለሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው በዚሁ የሁለት ቀናት መድረክ ከ106 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ ሴት አመራሮችና አባላት እየተሳተፉ ነው። የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ አመራሮቹና አባላቱ በነሐሴ 2012 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲይዙ ያለመ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባል ወይዘሪት ብዙወርቅ ከተተ ለኢዜአ እንደገለጹት መድረኩ የተዘጋጀው በአዋጁ ላይ በፊት ከነበረው አዋጅ በተለየ የተቀየሩ ነገሮችን ለሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለማስተዋወቅ ነው። በተለይም አዋጁ ሴቶች በምርጫው ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ሊያሳድጉ የሚችሉባቸው አንቀጾች ተካተውበታል ብለዋል። ሴት አመራሮችን በምርጫው በተሻለ መልኩ ለሚያሳትፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቦርዱ የሚደረግላቸው የፋይናንስ መጠንም ከፍ እንደሚል ተናግረዋል። አዋጁን ተከትለው እየወጡ ያሉ መመሪያዎች ሲጸድቁም የሴቶችን ተሳትፎ የሚያሳድጉ ስራዎች በውስጣቸው እንደሚኖሩም ገልጸዋል። የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ከሴት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሚገኙ ሀሳቦች እንደ ግብአት የሚወሰዱበት የመማሪያ መድረክም ነው ብለዋል። መሰል መድረኮችም በቀጣይ ጊዜ እንደሚዘጋጁም ጠቁመዋል። ዘንድሮ አገራዊ ምርጫ ለስድስተኛ ጊዜ እንደሚካሄድ ይታወቃል።