ቀጥታ፡

የፖሊስ ሰራዊት ለሀገራዊ ለውጡ ፍሬያማነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መመሪያ ተሰጠ

ኢዜአ ታህሳስ 19 / 2012  የፖሊስ አባላት ሰላምና ፀጥታ የማስፈን ስራቸውን በኃላፊነት መንፈስ በመወጣት ሀገራዊ ለውጡ ፍሬያማ እንዲሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስገነዘቡ። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ለ29ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን የፖሊስ ልዩ ሃይል አባላት ዛሬ አስመርቋል። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በስነ- ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ከዳር እንዲደርስና ፍሬያማ እንዲሆን ለሰላምና ፀጥታ መስፈን በትኩረት እየተሰራ ነው ። መንግስት የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና የለውጡ ጉዞ ከዳር ለማድረስ የፀጥታ ኃይሉን በአዲስ መልክ እያደራጀ መሆኑን ተናግረዋል ። "በለውጡ የተገኘው ነጻነት የሚረጋገጠው የህግ የበላይነት ሲከበር በመሆኑ ልዩ ኃይሉ ይህንኑ እንዲያሳካ ተልዕኮ ተሰጥቶታል" ብለዋል ። የፖሊስ ሰራዊቱ የሚጠበቅበትን ግዴታ እንዲወጣ በየደረጃው የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግለት ጠይቀዋል። የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት ሙያው የሚጠይቀውን ስነ- ምግባር በመጠቀምና በብቃት በመወጣት ሀገራዊ ለውጡን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የማሸጋገር ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣና የህግ የበላይነት እንዲከበር የክልሉን ፖሊስ ልዩ ኃይል በአዲስ መልክ ማደራጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል። "የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ካልተቻለ ሀገሪቱ ሰላም ልትሆን አትችልም" ያሉት ኮሚሽነሩ ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በብቃት እንዲወጡ አስገንዝበዋል። "የፖሊስ ሰራዊት ዋና ዓላማና ተልዕኮ የክልሉን ፀጥታ ማስከበርና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ነው" ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጌታቸው ኢታና ናቸው ። ኮሌጁ ለ29ኛ ጊዜ በሁርሶ፣ አላጌ፣ አዋሽ ቢሾላና በሰንቀሌ ማዕከላት ያሰለጠናቸውን የፖሊስ ልዩ ሃይል አባላት ዛሬ ማስመረቁን አስታውቀዋል ። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ተመራቂዎች በህገ- መንግስት፣ በውጊያ ታክቲክ፣ በአድማ ብተናና በሌሎች ወታደራዊ ሙያዎች የተሰጣቸውን ስልጠና በአግባቡ ያጠናቀቁ ናቸው። ከተመራቂዎቹ መካከል ኮንስትብል ናጂ ሀሰን በሰጡት አሰተያየት በስልጠና ቆይታቸው ባገኙት እውቀትና ክህሎት በመታገዝ በክልሉ ሰላምና ፀጥታን የማስፈን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም