ቀጥታ፡

ሰልፍ በወጡ ኢትዮጵያዊያን ላይ በደረሰው የቦንብ ጥቃት ማዘናቸውንና እንደሚያወግዙ የባህር ዳር፣ ደሴ፣ አሶሳ ፣መቀሌና ደብረ ብርሃን ነዋሪዎች

ደሴ /ባህር ዳር/አሶሳ /መቀሌ/ደብረ ብርሃን ሰኔ 16/2010 የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ አዲስ አበባ  ሰልፍ በወጡ ኢትዮጵያዊያን ላይ በደረሰው  የቦምብ ጥቃት ማዘናቸውን የባህር ዳር፣ ደሴ፣አሶሳ ፣መቀሌና ደብረ ብርሃን ነዋሪዎች ገለፁ። የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እታለማሁ በሽር እንደገለፁት በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት የመላው ኢትዮጵያውያንን ልብ የነከና ያሳዘነ ተግባር ነው። ኢሰብአዊ ድርጊቱን የፈፀሙት ግለሰቦች የኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ፣ ጥላቻና በቀል እንዲነግስ ቀን ከሌት ሳይታክቱ የሚሰሩ አካላት እኩይ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ጋሻው ጉግሳ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው "ድርጊቱ የበለጠ በጽናት እንደንዘልቅና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንድንቆም የሚያደርግ ነው" ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አንዳርጌ አለማየሁ እንዳሉት ''የተፈፀመው የቦንብ ጥቃት የዶክተር አቢይ አህመድን የለውጥ ሂደት ያልተቀበሉና በህዝቦች መካከል አሁንም አለመተማመን እንዲፈጠር የሚጥሩ አካላት እንዳሉ ማረጋገጫ ነው'' ብለዋል። ይህም ለውጡን የማይቀበሉ ሃይሎችና ኢትዮጵያ ወደቀደመ አንድነቷና ገናናነቷ እየተመለሰች መሆኗ እረፍት የነሳቸው ኃይሎች የፈፀሙት ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስቴር ደክተር አብይ አህመድን የለውጥ እንቅሰቃሴ ለመደገፍ አዲስ አበባ ውስጥ ሰልፍ በወጡ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት እንደሚያወግዙ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችና የስራ ኃላፊዎች ገለፁ። የትግራይ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ደክተር አብረሃ ኪሮስ እንደገለፁት ማንኛውም ዜጋ የሚወደውን መደገፍ የማይፈልገው መቃወም ህገ መንግስታዊ መብቱ ነው፡፡ ለመሪያችን ያላቸው ድጋፍ ለመግለፅ በወጡ ዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦች በህገ መንግስት የተረጋገጠውን ይህን የህዝቦች መብት የሚፃረሩ መሆናቸውን በድርጊታቸው አሳይተዋል የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ቄስ አርአያ ካሳ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመደገፍ በወጡ  የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ላይ የተፈፀመው የቦምብ ጥቃት እንደሚያወግዙት ገልፀዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተግባር በሃይማኖትም የሚወገዝ መሆኑን ገልፀው ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስተሩ የለውጥ እርምጃዎች ድጋፍ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ ለህዝቦች አንድነት እየተጠናከረ መምጣት ማሳያ ነው ሲሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። የአሶሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ቴዎድሮስ አበራ ሰልፉን በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበረና በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት መከታተላቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን እንዲያጠናክር እንዲሁም ይሄ ክልለ የኔነው መባባል አቁሞ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ እንዲያጠነጥን ማስገንዘባቸው ይበልጥ እንዳስደሰታቸውም አመልክተዋል፡፡ አቶ ቴዎድሮስ እንዳሉት በአዲስ አበባ ከተማ የተደረገው የድጋፍ ሠልፍ የሁሉም ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ሃሳብ የተንጸባረቀበት ነው። ፍቅር፣ አንድነት፣ መተባባርና ይቅር መባባል በተገለፀበት የድጋፍ ሠልፍ ላይ ፍንዳታ ተከስቶ በዜጎች ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት በመድረሱ በእጅጉ ማዘናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ብሄራዊ መግባባትና የውጭ ግንኙነትን ለማጠናከር የጀመሩትን የልማት ጉዞ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ያገባል ያሉት ደግሞ የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪ መምህር ሙሉጌታ ክፍሌ ናቸው። በሰልፉ ኢትዮያዊነት፣ አድነት፣ አብሮነት፣ ይቅርባይነት፣ ፍቅርና መቻቻል የሚዘመርበት  ሆኖ እያለ ይህን መሰል አሰፋሪ ተግባር መፈፀም አሳዛኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሌላው የ06 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጳጳስ በጋሻው ዛሬ አገራዊ አንድነትን፣ ልማትን፣ ፍቅር፣ የይቅርባይነትን ሀሳብ አንግበው አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት የሚወገዝ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ''የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት የሚያደናቅፉ ህይሎችን መንግስትና ህዝብ ተከታትሎ በመያዝ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድም ያሻል'' ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያከናወኑት ያለውን ስራና እያመጡት ያለውን ለውጥ ወደኋላ ለመቀልበስ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላትንም መንግስት ተከታትሎ በመያዝ ለህግ እንዲያቀርባቸው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም