ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሁለት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች ሊከፍት ነው፡፡ - ኢዜአ አማርኛ
ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሁለት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች ሊከፍት ነው፡፡
ኢዜአ ታህሳስ 19/2012 የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በሦስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ሁለት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች እንደሚከፍት አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው የመካኒካል ኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጅ አካዳሚክ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ያንቱ ምስጋና ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ በማኑፋክቼሪግ ኢንጅነሪንግ እና በኢንዳስትርያል ማኔጅመንት ሲስተም የዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት መርሀ ግብሮች ለመክፈት ዝግጅት አጠናቋል። አዲስ የሚከፍታቸው የትምህርት መርሃ ግብሮች ዩኒቨርሲቲው በዶክትሬት ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት መርሀ ግብሮች ከ14 ወደ 16 እንደሚያሳድገው ገልፀዋል፡፡ በሁለቱ የትምህርት መስኮች የተቀረጸው ስርዓተ ትምህርት መጽደቁን ጠቁመው በዘንድሮው ዓመት የሁለተኛ አጋማሽ የትምህር ዘመን መጀመርያ ላይ ከ10 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር ስራ እንደሚጀምር ተናግረዋል። በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የመካኒካል እንጅነሪንግና ቴክኖሎጅ ድፓርትመንት ሃላፊ አቶ ጉቱ ኦፍጋአ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱና በአካባቢው ያለውን የቴክኖሎጅ ሽግግር ፍላጎት መሰረት በማድረግ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን በመክፈት በቴክኖሎጅ ዙሪያ ያለውን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ መምህር ዶክተር ጉተታ ቃበታ እንደተናገሩት በወለጋ ዩኒቨርሲቲ እየተከፈተ ያለው አዲስ የዶክተሬት ድግሪ የትምህርት መርሃ ግብር በሀገርቱ የሚታየውን የተማረ የሰው ሃይል እጥረት ለመቅረፍ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡