ቀጥታ፡

ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ አሉታዊ መልዕክቶች ሰለባ እንዳይሆኑ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይገባል ተባለ

ኢዜአ ታህሳስ 18 ቀን 2012 ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ በሚተላለፉ አሉታዊ መልዕክቶች ሰለባ ከመሆናቸው በፊት አስቀድሞ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ። ይህ የተገለጸው በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት ለከተማዋ ወጣቶች በማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃላይ ላይ ገለጻ በተደረገበት ወቅት ነው። የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ አጠቃላይ የመገናኛ ብዙሃን አሰራርና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ ውይይት ተደርጓል። በዚሁ ወቅትም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሚታዩት አለመረጋጋቶች፣ የሰውና ንብረት ውድመቶች አንዱ ምክንያት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩት ያልተረጋገጡና የሀሰት መረጃዎች መሆናቸው ተመልክቷል። ወቅቱ በእጅጉና በፍጥነት የሚለዋወጡ ሁኔታዎች የሚከሰቱበት በመሆኑ በተለይ ወጣቱ መንቃት አለበት ሲሉ በውይይቱ ላይ መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት መምህር አቶ ኑቱማን አሊዪ አሳስበዋል። አቶ ኑቱማን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወጣቶች ለህይወታቸው ጠቃሚና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በመተው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ተጠምደዋል ሲሉም ተናግረዋል። በዚህም ወጣቶች በእነዚህ መገናኛ አውታሮች በሚተላለፉ አፍራሽ መልዕክቶች እየተጠለፉ ራሳቸውንም አገርንም እየጎዱ መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩ የኢትዮጵያ ብቻ አለመሆኑን የሚያብራሩት አቶ ኑቱማን ''በህንድና ናይጄሪያ ወጣቶች በማሕበራዊ ሚዲያ በሚተላለፉ መልዕክቶች ተነሳስተው ከፍተኛ ጥፋት ፈጽመዋል'' ነው ያሉት። በኢትዮጵያ በዚሁ ማሕበራዊ ሚዲያ በሚተላለፉ መልዕክቶች ወጣቶች በተለያዩ አካባቢዎች መጥፎ ጠባሳ የጣሉ ጸያፍ ተግባራትን መፈጸማቸውን አልሸሸጉም። ወጣቶች የዚህ ችግር ሰለባ እንዳይሆኑ አስቀድመው የመረጃውን ትክክለኛነት መመርመርና ከሌሎች ታማኝ ምንጮች ማመሳከር እንደሚጠበቅባቸው መክረዋል። ወጣቶች በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ የተሰራጨው መረጃ ትክክለኛ ሆኖ ቢገኝ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቅ እንዳለባቸውም ተመልክቷል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተወከሉት አቶ በላይነህ አቅናውም እንዲሁ ወጣቶቹ መሰል አደገኛ መረጃዎች ሲመለከቱ ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የተሰራጨው መረጃ ሊሆን የሚችል መሆኑን መመርመር፣ በተጨባጭ መረጃ የታገዘ መሆኑን ማረጋገጥና ትክክለኛ ምንጭ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው ሲሉ ነው አቶ በላይነይ ምክራቸውን የለገሱት። ከዚህ ጎን ለጎን መንግስት የብሮድካስት ባለስልጣንን የመቆጣጠሪያ መንገድ ማጥበቅ እንዳለበትም  ተናግረዋል። የፌስቡክ ኩባንያም በኢትዮጵያ በአምስት ቋንቋዎች የሚሰራጩትን መረጃዎች ለመቆጣጠር ሰራተኞችን ለመቅጠር ሃሳብ እንዳለው አቶ በላይነህ አስረድተዋል። በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶችም የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሩ ጠቃሚና የተወሰንም ንቃት እንደፈጠራለቸው ይናገራሉ። ተመሳሳይ መርሃ ግብሮች ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ቢዘጋጅ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚሰራጩ ሀሰተኛና የጥፋት መረጃ ሳቢያ አሁን ያንዣባበውን አደጋ መቀነስ እንደሚያስችል ጠቁመዋል። በተጨማሪም ወጣቶቹ በመገናኛ ብዙሃን በኩል አደገኛ የሆኑ ዘገባዎች እየተላለፉ በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም