በጣና ሀይቅ የቅርስ ዘረፋን ለመከላከል የፖሊስ ባህር ኃይል ሊቋቋም ነው

63

ኢዜአ ታህሳስ 18 ቀን 2012 በጣና ገደማት የቅርስ ዘረፋ እንዳይፈጸም ለመከላከል የክልል የፖሊስ የባህር ኃይል የማቋቋም ስራ መጀመሩን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አላምረው ለኢዜአ እንደገለጹት የሚቋቋመው የፖሊስ የባህር ኃይል በጣና ሀይቅ ላይ የሚገኙና እድሜ ጠገብ የቅርስ ሀብቶችን የያዙ 31 ገዳማትን ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው፡፡

"የጣና ገዳማት ሀገሪቱ ካሏት ታላላቅና ውድ መንፈሳዊና ባህላዊ ቅርሶች መካካል ግንባር በመሆናቸው ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል" ብለዋል ።

የቱሪዝም ዘርፉን ሰፊ የስራ እድል መፍጠሪያና የገቢ  ምንጭ ለማድረግ በክልሉ መንግስት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በአቅጣጫው መሰረት የኢንቨስትመንትና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን የሚጠብቅ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፖሊስ በቅርቡ በክልል ደረጃ መቋቋሙን ጠቅሰዋል፡፡

"የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲጠብቅ ተልእኮ የተሰጠው ይኸው የፖሊስ ኃይል በባህር ላይ ጀልባዎች ጭምር የታገዘ ጥበቃ ለማድረግ እንዲያስችለው ለአባላቱ ልዩ ስልጠና ይሰጣቸዋል" ብለዋል፡፡

በጣና ሀይቅ ላይ እስከ 35 የሚደርሱ ገዳማትና አብያተ-ክርስቲያናት እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም