በጎፋ ዞን ኮሌራን የመቆጣጠር ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጎፋ ዞን ኮሌራን የመቆጣጠር ስራ እየተካሄደ ነው
ኢዜአ ታህሳስ 18 ቀን 2012 በጎፋ ዞን የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ የመቆጣጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቀ። በሽታው አጎራባች በሆኑ ጋሞ ዞን ካምባ እና ደቡብ ኦሞ ዞን ማለ ወረዳዎች ምልክቱ በመታየቱ የቁጥጥር ስራው በቅንጅት እየተካሄደ መሆኑ ተመልከቷል። በቢሮው የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ እንዳሻው ሽብሩ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በተከሰተው በሽታ 180 ሰዎች ተጠቅተዋል ። በሽታው በናሙና ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ቡድን በማቋቋም በቦታው ሆኖ የህክምና አገልግሎትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። በሽታውን ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ጥረት መድኃኒትምም ሆነ የህክምና ግብአት እጥረት አለማጋጠሙን ተናግረዋል በበሽታው ተጠቅተው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ በተደረገላቸው ህክምና አገግመው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል። በበሽታው ቁጥጥር ስራ ለተሰማሩ 35 ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ስልጠና መሰጠቱንና ሴክተር መስሪያ ቤቶችም በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። "ትምህርት፣ ውሃ ፣ ግብርናና ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች የታቀፉበት የቁጥጥር ስራ እየተካሄደ ነው" ያሉት ደግሞ የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ በቀለ ናቸው። በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የሚመራ የጋራ ግብረ ኃይል በማቋቋም የቁጥጥር ስራው እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። እንደ ኃላፊው ገለጻ የክልሉ ጤና ቢሮ የመድኃኒት፣ ኬሚካልና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ ነው። በጎፋ ዞን ቀደም ሲል በተከሰተው በዚሁ በሽታ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።