ቀጥታ፡

በሶማሊያ ርእሰ መዲና ሞቃዲሾ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች ሞቱ

ኢዜአ ታህሳስ 18/2012 በሶማሊያ ርእሰ መዲና ሞቃዲሾ ዛሬ ጠዋት በመኪና ላይ በተጠመደ የቦምብ ጥቃት ከ60 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ። በመዲናዋ አውቶብስ ፍተሻ ጣቢያ አካባቢ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት ከ90 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን የአገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል። በአደጋው አሰቃቂ ሁኔታ የሰዎች ህይወት እንዳለፈ የአይን እማኞች ያረጋገጡ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተነግሯል። ፍዳታው በአጥፍቶ ጠፊዎች መከሰቱን የቻይና ዜና አገልግሎት ዥንዋ የአገሪቱን የመንግስት ቃል አቀባይ እስማኤል ሙክታርን ጠቅሶ ዘግቧል። ከሞቱት አብዛኞቹ ተማሪዎች መሆናቸውን ቃል አቀባዩ ጨምረው የገለጹ ሲሆን የቆሰሉት ወደህክምና መስጫ ተቋማት ተወስደዋል። በጥቃቱ የተጎዱት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ሌሎች ንፁሃን ዜጎችና የፀጥታ ሰራተኞች ናቸው። ጥቃቱ የተፈፀመው በከተማው የቀረጥ መቆጣጠሪያና የድንተኛት ፍተሻ ጣቢያ አካካቢ መሆኑም ተነግሯል። የፀጥታ ሰራተኞች ቦንብ ተጠምዶ የነበረበትን መኪና ለመፈተሽ ሲሞክሩ ፍንዳታው እንደተከሰተ መረጃዎች አመልክተዋል። የአይን እማኞችም በገቢ ቢሮው አካባቢ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ እንደሰሙ በመግለጽ ጥቃቱ ቢሮው ላይ የተቃጣ ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ገልጸዋል። ለጥቃቱ እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም በሶማሊያ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት በመፈፀም የሚታወቀው አልሸባብ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት መኖሩም ተመልክቷል። አልሸባብ ከአንድ ወር በፊት ሞቃዲሾ ከተማ በሚገኝ ታዋቂ ሆቴል ላይ በፈጸመው ጥቃት 4 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም